ሙስሊም ክርስቲያኑ ከጥንት ጀምሮ የነበራቸውን የመከባበርና መደጋገፍ እሴቶችን ማስቀጠል እንዳለባቸው ተገለጸ

102

ወልዲያ ፤ ሚያዝያ 24/2014 (ኢዜአ) ሙስሊም ክርስቲያኑ ከጥንት ጀምሮ የነበራቸውን የመከባበርና መደጋገፍ እሴቶች አጠናክረው በማስቀጠል ለልጅ ልጆቻቸው እንዲተርፍ ማድረግ እንዳለባቸው ተገለጸ።

1ሺህ 443ኛው ኢድ አልፈጥር በዓል በወልዲያ ከተማ በደማቅ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓት ተከበሯል።

የወልዲያ ከተማ መስጂዶችና እስላማዊ ትምህርት ቤቶች ስራ አስኪያጅ  ሃጂ ሲራጅ አደም በወቅቱ  እንዳሉት፤  ሙስሊሙ ህብረተሰብ ከክርስትና እምነት ተከታይ ወንድምና እህቶቹ ጋር በአንድ ማዕድ ቆርሶ በመብላት ፍቅርን ተላበሶ የኖረ ነው።

በዚህ ትብብርም ሙስሊሙ ቤተ- ክርሲቲያን፤  ክርስቲያኑ ደግሞ መስጊድ በመገንባት አጋርነታቸውንና ፍቅራቸው በተግባር ማስመስከራቸውን ጠቅሰዋል።

ዛሬም ቢሆን ጥንት የነበረው የመከባበርና የመደጋገፍ እሴቶቻችን  አጠናክረን በማስቀጠል ለልጅ ልጆቻችን እንዲተርፍ  በመስራት ለሃገራችን ዘላቂ ሰላም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

በበዓሉ አከባበር ሥነሥርዓት ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዶክተር ዳዊት መለሰ ፤  ሙሲሊሙ ህብረተሰብ ይህን ታላቅ በዓል ሲያከብር ችግረኞችን በመጎብኘት  በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

እንደ ቀደሙ አባቶቻችን ትውልዱ ጤናማና ለሃገር ሰላም ዘብ የሚቆም እንዲሆን መንፈሳዊ ምክራቸው ዘወትር ተጠናክሮ እንደቀጠለም አመልክተዋል።

የበዓሉ ተሳታፊ ወይዘሮ እማዋይሽ ካሳው በሰጡት አስተያየት፤ የዘንድሮውን በዓል እያከበርን ያለነው በልዩ ፍቅርና መከባበር ነው ብለዋል፡፡

”ከዋዜማው ጀምሮ ክርስቲያን ጎረቤቶች በዝግጅት እያገዙኝ ዛሬም በአንድ ላይ ደስታችንን የምናሳልፍበት የፍቅር ቀናችን ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ይህን ፍቅራችንን ለመናድ በውስጣችን ገብተው ሰላማችንን ለማናጋት የሚጥሩ ሁሉ አደብ ሊገዙና   በተለይም እኛ እናቶች ወጣት ልጆቻችን ልንመክር ይገባል ነው ያሉት።

አሁን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በእምነቶች መካከል እየገቡ ሀገር ለማተራመስ የሚጥሩ ቡድኖች አይሳካላቸውም ያሉት ደግሞ አቶ ሃሰን አረቡ ናቸው።

እኩይ ዓላማ አንግበው ህዝብን ከህዝብ ለማለያየት የሚጥሩ አጥፊዎች  ህዝቡ ሊታገላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በወልዲያ ከተማ  የኢድ አልፈጥር በዓል በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በሶላትና ስግደት በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን የኢዜአ ሪፖርተር ከሥፍራው ዘግቧል።