የሃይማኖት ልዩነትን ለግጭት ምክንያት የማድረግ ሙከራን ታሪካችን የማይፈቅድ በመሆኑ ብዝሃነታችን ልናከብር ይገባል - የሲዳማ ክልል መንግስት

149

የክልሉ መንግስት ባወጣው መግለጫ የአገራችን ኢትዮጵያ የብሔሮች እና የሃይማኖቶች ብዝሃነት ያለባት ሀገር ነች ብሏል።እነዚህ ልዩነቶች በአንዳንድ ሀገራት የመለያየት እና የመጠፋፋት መነሻ ሲሆን የኢትዮጵያ ታሪክ ግን ከዚህ ፍጹም የተለየና የአንድነቷና የውበቷ ምክንያት ነው ሲል ገልጿል።

ኢትዮጵያ ሀገራችን የእስልምና እና የክርስትና ሃይማኖቶችን አቅፋ የያዘች ሁሉም ሃይማኖቶችን በእኩልነት የምታስተናግድ የሁለቱም እምነት ተከታዮች የየራሳቸውን እምነት ይዘው በሰላም ተከባብረው የሚኖሩባት ሀገር ነች ብሏል።

ከዚህ ሲያልፍ በተለያየ ሃይማኖት ውስጥ ቢሆኑም ወንድምና እህት መሆናቸውን አውቀው አንዱ የሌላውን እምነት ሳይጫን በመረዳዳት፣ በመቻቻል፣ አብሮ በመብላትና በመጠጣት ለዓለም ህዝብ ተምሳሌት የሚሆን እሴት ገንብቶ የጋራ ሀገሩን በጋራ ሲገነባና ሲጠብቅ መኖሩን ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ከፍታ የሚያሰጋቸው አለፍ ሲልም በእኛ ኪሳራ ሲበለጽጉ የነበሩ ጥቅማቸው የሚቀርባቸው ወገኖች ሁሉ ተባብረው አገራችንን ለመበታተን ብዙ ቢጥሩም ህዝቦች በአንድነት ቆመው በመከላከላቸው ሴራቸው አልተሳካላቸውም በማለት ገልጿል።

ይሁንና በዓለም ህዝብ ፊት የተሸነፉ የውስጥና የውጪ ጠላቶቻችን ከሰሞኑን የሃይማኖት ግጭት በማስነሳት አገራችንን የደም ምድር ለማድረግ፣ ህዝባችንን የሞትና ሰቆቃ ገፈት ቀማሽ እንዲሆን እና ሀገር የመበተን ህልማቸውን እውን ለማድረግ ሌተ ቀን እየተረባረቡ ይገኛሉ ያለው መግለጫው፤ ህዝባችን ይህንን ጠንቅቆ በመረዳት ከመከፋፈል ይልቅ ለብዙ ሺህ ዓመታት በገነባው በአብሮነት እሴት አንድነቱን በማጠናከር ከፋፋይ አካሄዶችን በየቤተ እምነቱ ማውገዝና ማጋለጥ ይኖርበታል ብሏል።

መንግሥታችን የጠላቶቻችን ተልዕኮ በመቀበል በሃይማኖት ሰበብ ግጭት ያስነሱትን እንዲሁም እያስፋፉ የሚገኙ ወገኖችን ከህዝቡ ጋር በመሆን አድኖ ለፍርድ እንደሚያቀርባቸው እየሰራ ነው ብሏል።

ከታሪካችን ጋር የማይሄድ በሃይማኖት ሽፋን የሚደረግ ማናቸውንም ግጭት ቀስቃሽና አባባሽ ሁኔታ አጥብቀን እንቃወማለን ብሏል መግለጫው።

እስካሁንም በዚሁ ሰበብ የሰው ህይወትና ንብረት እንዲወድም ያደረጉ ቡድኖችን በጽኑ ያወገዘው መግለጫው፤ በተፈጠረው ችግር ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች መጽናናትን ተመኝቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም