መንግሥት ለከልበቲ ረሱ ዞን ተፈናቃዮች እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል

109

ሠመራ ሚያዝያ 24/2014(ኢዜአ) ... በአሸባሪው ህወሓት ወረራ በአፋር ክልል ከልበቲ ረሱ ዞን ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የክልሉ መንግሥት አስፈላጊዉ ድጋፍ ሁሉ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ አስታወቁ፡፡


በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ከከልበቲ ረሱ ዞን ተፈናቅለው በሰመራ ከተማ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ የማእድ ማጋራት ሥነሥርዓት ተካሂዷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በሥነሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት የክልሉ መንግሥት ለከልበቲ ረሱ ዞን ተፈናቃዮች እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል።


በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ከተጎዱ አካባቢዎችና የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል የከልበቲ ረሱ ዞን ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው ብለዋል።


የሽብር ቡድኑ ከኅብረተሰቡ በገጠመው የጀግንነት ተጋድሎ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበት ያሰበውን ማሳካት ሳይችል ቀርቷልም ሲሉ ገልጸዋል።

የዞኑ ማህበረሰብ ማንነቱን፣ ሉዓላዊነቱን፣ ክብሩን ለማስጠበቅ እና ለማረጋገጥ የከፈለው ውድ ዋጋ በትውልድ ሲዘከር እንደሚኖርም ተናግረዋል።


የክልሉ መንግሥትም ለዞኑ ማህበረሰብ ከአስቸኳይ ጊዜ ሰብዓዊ ድጋፍ እስከ መልሶ ማቋቋም ድረስ መላ ኢትዮጵያውያን ባሳተፈ አግባብ በመንቀሳቀስ አስፈላጊ ድጋፍ ሁሉ ያደርጋል ብለዋል።

የኢድ አልፈጥር በዓል የፍቅር የመረዳዳት፣ የአብሮነትና ወንድማማችነት መገለጫ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጸው ዛሬ የተደረገው ማዕድ ማጋራትም የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች በዓሉን ተደስተው እንዲያሳልፉ ለማድረግ ተመሳሳይ መርሃ ግብር ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድር አወል በዓሉ ለመላ ኢትዮጵያውያን የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነትና የአንድነት እንዲሆንላቸው መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

በሥነሥርዓቱ ከታደሙ ተፈናቃይ ወገኖች ሀጂ ሳሊህ መሀመድ እንዳሉት የክልሉ መንግሥትና የአካባቢው ማህበረሰብ የሳያቸው ፍቅርና አብሮነት በዓሉን ተደስተው እንዲያሳልፉ አድርጓቸዋል።


በተለይም ርዕሰ መስተዳድር አወል በዓሉን አብረዋቸው በማሳለፍ ለወገኖቻቸው ያላቸውን አክብሮት በተግባር ያሳዩበት መሆኑን ገልጸዋል።


ረመዳን ወርን ጨምሮ በዓሉን የአካባቢው ህብረተሰብ ያደረገላቸው ድጋፍና እገዛ ትልቅ ክብር የሚገባው ነው ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ፋጡማ ሙሳ ናቸው።


የክልሉ መንግሥት ለበዓሉ እርድ አዘጋጅቶ ጭምር በዓሉን በደስታ እንድናከብር ማድረጉ እቤታችን ያለን ያክል እንዲሰማን አድርጎናል ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባን ጨምሮ የክልሉ መንግሥት የሥራ ሀላፊዎች በጊዜያዊ መጠያ ጣቢያዎች ከሚገኙ ወገኖች ጋር በዓሉን ማሳለፍቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም