በኃይማኖት ሽፋን ስም የድሬዳዋን እና የአገርን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች የሚያውኩ ላይ አስፈላጊ እርምጃ ይወሰዳል

111

በኃይማኖት ሽፋን ስም የድሬዳዋን እና የአገርን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ለማወከ የሚደረግ ያልተፈቀደ ሰልፍና የቡድን ሁከት በሚፈጥሩ አካላት ላይ አስፈላጊ እርምጃ ይወሰዳል ሲል የድሬዳዋ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ፡፡

ለዘመናት በአንድነትና በጋራ የተሻገሩትን የአገሪቱን ዜጎች ኃይማኖትን ተገን በማድረግ የሚደረጉ የሽብር ተግባራት እና የእርሰ በርስ ሁከትና ነውጥ ለመፍጠር የሚከወኑ ተግባራት መቼም ቢሆን አይሳኩም።

አንዴ በብሔር፣ በስልጣን፣ በምርጫ ሌላ ጊዜ እና ዛሬ ደግሞ በኃይማኖት ሽፋን የተጀመረው ሁከትና የእርስ በርስ ግጭት የመፍጠር ህመምና ጫፍ የረገጠ በሽታ በኢትዮጵያ ምድር አይሳካም።

ኃይማኖትና ብሔርን ሽፋን በማድረግ ሰሞኑን ፅንፍ የወጣው ተግባር አንድም የተደበቀ ስልጣንን ለማግኘት አንድም የአገሪቱን ብልፅግና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ወደኋላ ለመጎተት የተሴረ እኩይ እና የተወገዘ ተግባር ነው።

ባለፈው የተቀደሰ የአርብ ስግደት ማብቂያ ላይ በድሬዳዋ የተከሰቱት ትዕይንቶች የዚሁ መገለጫ ናቸው።

ችግሩን የአስተዳደሩ አመራሮች፣ ህዝብ፣ የፀጥታው አካል ይበልጥኑ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ተረባርቦ በቁጥጥር ስር ባያውለው ኖሮ ሌላ መልክ ይይዝ ነበር።

ችግሩን በጊዜያዊነት እና በዘለቄታ ለመፍታት የአስተዳደሩ ከንቲባ የሚመራው የፀጥታ ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ በማካሄድ ከሚያዝያ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ያልተፈቀደ የጎዳና ሰልፍ የቡድን ጉዞ ማድረግ መከልከሉን ወስኗል።

ይህን ውሳኔ ተላልፈው በሚገኙ አካላት አስፈላጊውን እርምጃ ይወሰዳል ።

ለመላው የአስተዳደሩ ነዋሪዎች እንኳንም ለ1443ተኛ የኢድ አልፈጥር በአል አደረሳቹ እያለ የተጀመረውን የሰላም፣ የአብሮነትና የብልፅግና ጎዳና ዳር ለማድረስ በጋራ የእንረባረብ ጥሪውን ያስተላልፋል ።

የድሬዳዋ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ