ሰላም ከሌለ ሁሉ ነገር ይቃወሳል - የአፋር ክልል መንግስት

266

ሚያዚያ 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሰላም ከሌለ ሃይማኖትን በአግባቡ መከወን ይከብዳል፣ ሰላም ከሌለ ስለ ብልፅግና ማውራት ይከብዳል፣ ሰላም በአካባቢያችን በውስጣችን ከታጣ ሁሉ ነገር ይቃወሳል ሲል የአፋር ክልል መንግስት ገለጸ።

በመሆኑም ውስጣችንን፣ አካባቢያችንና ሀገራችንን ብሎም አለማችንን ሰላማዊ ለማድረግ የእያንዳንዳችን ድርሻ የማይናቅ ሚና ስለሚጫወት ቅድሚያ ለሰላም መስጠት ይጠበቅብናል ሲል መግለጫ ሰጥቷል።

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ በሰጠው መግለጫ፤ በሀገራችን በየትኛውም አካባቢ የሚከሰቱ ኢ-ፍትሀዊና ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች በማንም ይፈፀም በማንም ሊወገዝ እና ጥፋተኞች በጥፋታቸው ልክ ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል ብሏል።

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

የኢድ አል ፈጥር በዓል የሶላት ስነ-ስርአት በአፋር ክልል ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተጠናቋል።

በዛሬው ዕለት የተከበረው 1 ሺህ 443 ሂጅራ የኢድ አል ፈጥር የሶላት ስነ ስርአት በአፋር ክልል ሰላማዊ በሆነ መልኩ የተጠናቀቀ ሲሆን ህዝቡ የተቸገሩን በመርዳት በተለይም በጁንታው ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ጋር በጋራ በመሆን ኢዱን በማሳለፍ ላይ ይገኛል።

ኢዱ ከወትሮው በተለየ መልኩ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በማሰብ አለኝታነትን በማሳየት ኢዱን በጋራ በደስታና በአብሮነት ስሜት እያሳለፉ ነው።

ህዝቡ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር በማሳየት ሁሉም በየአካባቢው ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ወንድም የወንድሙ ጠባቂ መሆኑን በማስመስከር ላይ የሚገኝ ሲሆን ስለ ሰላም መስራት፣ ወደ ሰላም ጥሪ ማድረግ፣ ሰላምን መኖርን በማሳየት ላይ ይገኛል።

ሰላም ለሁሉም ነገር ዋነኛ መሰረት በመሆኑ ሁላችንም በየአካባቢያችን የሰላም ባንዲራን ልናውለበልብ ይገባል።

ሰላምን ለማደፍረስ ሴራ የሚያሴሩ፣ ህዝብን ከተረጋጋ ኑሮው በማፈናቀል፣ በመግደል እና በማሳደድ ርካሽ የፖለቲካ ትርፍን ለማግኘት የሚያደርጉትን መሯሯጥ በጋራ በመሆን መግታት ግድ ይላል።

በሀገራችን በየትኛውም አካባቢ የሚከሰቱ ኢ-ፍትሀዊና ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች በማንም ይፈፀም በማንም ሊወገዝ እና ጥፋተኞች በጥፋታቸው ልክ ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል።

ይሁንና በየትኛውም ጫፍ ችግር ቢያጋጥም ችግሩን በማባባስ ሳይሆን ችግሩን አላህ በሚወደው መንገድ በሰከነ አእምሮ በቅንነት በመፍታት መረባረብ ማገዝ ይጠበቅብናል።

እሳት ላይ ቤንዝን ማርከፍከፍ ጀግንነት ባለመሆኑ ለጠላቶቻችን በር መክፈት እና የበለጠ ለአደጋ ተጋላጭ ከመሆን ያለፈ ትርፍ አያስገኝልንም።

ሰላም ከሌለ ሃይማኖትን በአግባቡ መከወን ይከብዳል፣ ሰላም ከሌለ ስለ ብልፅግና ማውራት ይከብዳል፣ ሰላም በአካባቢያችን በውስጣችን ከታጣ ሁሉ ነገር ይቃወሳል፣ በመሆኑም ውስጣችንን፣ አካባቢያችንና ሀገራችንን ብሎም አለማችንን ሰላማዊ ለማድረግ የእያንዳንዳችን ድርሻ የማይናቅ ሚና ስለሚጫወት ቅድሚያ ለሰላም መስጠት ይጠበቅብናል።

በመጨረሻም የኢድ አል ፈጥር በአል ሶላት በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸው ትልቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ባለ ድርሻ አካላት ላቅ ያለ ምስጋና እያቀረብን ሰላም የእለት ተለት ጉርስ በመሆኑ በዘላቂነት ሰላማችንን በማስጠበቅ ህዝባችን ከጥንት ጀምሮ ያዳበረውን ለሰላም ያለውን ትኩረትና ቅድሚያ መስጠት በማጠናከር ልንቀጥል ይገባል።

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት

ሚያዝያ 24/2014

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም