ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ለተወሰነ አካል ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉንም ዜጋ ትብብር ይጠይቃል

125

ሚያዚያ 24/2014/ኢዜአ/ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ለተወሰነ አካል ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉንም ዜጋ ትብብር እንደሚጠይቅ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ ገለጹ።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ ይህን ያሉት በአዲስ አበባ ስቴዲየም በተካሄደው የ1 ሺህ 443 ዓመተ ሂጅራ የዒድ አልፈጥር በዓል "ታላቁ የኢድ ሰላት" ላይ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ነው፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የእስልምና እምነት አባቶች፣ ጎረቤት አገራት እስልምና እምነት ተወካዮች፣ ከኢድ እስከ ኢድ ጥሪን ተቀብለው የመጡ የዳያሥፖራ አባላት እና በርካታ የእምነቱ ተከታዩች ተሳትፈዋል፡፡

በዚሁ ወቅት እንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ ህዝበ ሙስሊሙ ሊከባበር፣ ሊፈቃቀር እና አንድነት ሊኖረው ይገባል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥም በአንድነት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

"ሰላም የሚመጣው በተግባር ነው፤ ሰላም የሚመጣው በህዝብ ነው፤ ሰላም የሚመጣው በመንግስት ነው፤ በተወሰኑ ሰዎች ብቻ ሰላም ሊመጣ አይችልም " ሲሉም ሁሉም ዜጋ ለሰላም መስፈን ሚናውን እንዲወጣ  ጥሪ አቅርበዋል፡፡   


የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼክ ሱልጣን አማን ኤባ በበኩላቸው  መንግስት ሰሞኑን በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ችግሮች እጃቸው ያለበት ሁሉንም አካላትን ለህግ እንዲያቀርብ ጥሪ አቅርበዋል።

May be an image of 1 person

በወንድማማቾች መካካል ጠብ ለመፍጠር የሚሰሩ አካላት በፈጣሪም ሆነ በሰው ዘንድ ተቀባይነት እንደሌላቸው ሊገነዘቡ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡   

የእስልምና ሃይማኖት መምህር የሆኑት ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፤ "ክፋትን በክፋት፣ ጥፋትን በጥፋት እንድንመለስ የታዘዝን ህዝቦች አይደለንም" ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ህዝበ ሙስሊሙ የሚታወቀው በሰላም፣ ፍትህ፣ እኩልነት እና ለሌሎች ተስፋ በመሆን ነው ብለዋል፡፡

May be an image of one or more people and people standing

ይህ በጎ እሴት ዛሬም መገለጫችን ሆኖ ሊቀጥል ይገባል ያሉት ኡስታዝ አቡበከር ፤ ከዚህ አኳያ ህዝበ ሙስሊሙ በእስልምና አስተምህሮ መሰረት ለሰላም መትጋት እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ አቶ መለስ ዓለሙ፤ እስልምና መነሻው ሰላም፣ መዳረሻውም ሰላማዊነት ነው ብለዋል፡፡

May be an image of 4 people and people standing

ሙስሊሙ ማህበረሰብ በረመዳን ወር ያሳየውን መልካም ተግባር  በመጪው ጊዜም አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዜጎቿ ትብብር የተገነባች አገር ናት ያሉት አቶ መለስ፣ አሁንም በትብብርና አብሮነት አገራችንን ወደ ተሻለ ምእራፍ ማሻገር አለብን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም