ህዝበ ሙስሊሙ ሊከባበር፣ ሊፈቃቀር እና አንድነት ሊኖረው ይገባል

277

ሚያዚያ 24 ቀን 2014 (ኢዜአ) ህዝበ ሙስሊሙ ሊከባበር፣ ሊፈቃቀር እና አንድነት ሊኖረው እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ ጥሪ አቀረቡ።

ሃጂ ሙፍቲ ይህን ጥሪ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ስታድየም እየተከበረ በሚገኘው የኢድ ሰላት መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

በንግግራቸውም አንድነት፣ ሰላም፣ ልማት፣ ዕድገት ሁሌም ለኢትዮጽያ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

አንድነት በተግባር የሚገለጽ በመሆኑም ሁሉም ለአንድነት የሚችለውን ሁሉ ማበርከት እንዳለበት ገልጸዋል።

መንግስት ለሙስሊሙ ማህበረሰብ እያደረገ ላለው ትብብር እና ትኩረትም ምስጋና አቅርበዋል።የንጹሃን ደም መፍሰስ የለበትም፣ ንጹሃንም መፈናቀል የለባቸውም ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼክ ሱልጣን አማን ኤባ በበኩላቸው የዘንድሮውን ረመዳን ከኢድ እስከ ኢድ ጥሪን ተከትለው ከመጡ ኢትዮጵያውያን ጋር ስናከበር ቆይተናል ብለዋል።

ሰሞኑን በተለያዩ አከባቢዎች በተፈጠረው ችግር እጃቸው አለበት የሚባሉትን መንግስት ለህግ ሊያቀርባቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።

በአገሪቷ የሚታየው አለመግባባትም በውይይት እና መግባባት ሊፈታ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ታላቁ የዒድ ስግደት በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ይገኛል።

በአዲስ አበባ ስታድየም በመከበር ላይ በሚገኘው ታላቅ የዒድ ስግደት የእስልምና የእምነት አባቶች፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ከጎሮቤት አገራት የወጡ እንግዶች ፣ ዳያስፖራዎች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት እና የእምነቱ ተከታዮች በመሣተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም