ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚከሰቱ ችግሮችን ከማባባስ ይልቅ በመመካከር መፍታት ያስፈልጋል-----የሃይማኖት አባቶች

111

ሰቆጣ ሚያዝያ 23/2014 (ኢዜአ) ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚከሰቱ ችግሮችን ከማባባስ ይልቅ በመመካከር የሚፈቱበትን መንገድ መከተል ይገባል ሲሉ የዋግ ኽምራ ዞን ሃይማኖት አባቶች አመለከቱ። 
ኢዜአ ወቅታዊ ጉዳዮችን በማስመልከት በዋግ ህምራ ከሀይማኖት አባቶች ጋር ቆይታ አድርጓል።

የዋግ ኽምራ ሃገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ ሊቀ ህሩያን ሃይሌ አለሙ እንደገለፁት የውስጥና የውጭ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማፍረስና ለማተራመስ እቅደው ከሚንቀሳቀሱባቸው ተግባራት መካከል በተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮች መካከል ግጭት ማስነሳት ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ለበርካታ ዘመናት ተደጋግፈውና ተዋደው የኖሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የምእመኑን አብሮነት በመናድ በህዝብና በሀገር ላይ አደጋ እንዲከሰት የሚሰሩ የውስጥና የውጭ ጠላቶች መኖራቸውን ሊቀ ህሩያን ሃይሌ ተናግረዋል።

"አብረን ተዋደንና ተከባብረን ስንኖር ያለውን የሰላም አየርና የአገር አለኝታነት እያየን ነው" ያሉት ሊቀ ህሩያን ሃይሌ አብሮነቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊተባበሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

"በተለይ ወጣቱ አንድነቷ የተጠበቀ ሀገር ለመረከብ በዚህ ወቅት በተረጋጋ  መንፈስ  ለሰላም አብክሮ ሊሰራ ይገባል" ብለዋል።

"ከሰሞኑ በጎንደርእሱን የተከሰተው እኩይ ተግባር የጎንደር ህዝብ ታሪክና የአብሮነት ልምድ የሚመጥን እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ በጥቅመኞች የተዘወረ ጉዳይ እንደሆነ" አመልክተዋል።

ይህንን ተከትሎ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ መሰል ችግሮችን  ማባባስ  ጥቅም እንደሌለው በመረዳት የሀይማኖት አባቶች  በመመካከር ችግሩን መፍታትና አብሮነትን በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ ጠንክሮ መስራት አዋጭ መሆኑን መረዳት ይገባናል" ብለዋል። 

የሰቆጣ አንዋር መስጊድ ኢማም ሃጅ ሸህ አህመድ አደም በበኩላቸው "በጎንደር ከተማ የተከሰተው ድርጊት  አስነዋሪና የሚወገዝ ነው" ብለዋል።

ድርጊቱ ለዘመናት ተዋደውና ተደጋግፈው የኖሩትን የሁለቱ ሃይማኖቶች ተከታዮችን የማይወክል ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል።

"በሃይማኖቶቹ ተከታዮች መካከልም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ችግሮች ሲያጋጥሙ እንደ ቀድሞ አባቶቻችን ሁሉ በዱዓ ፣ በመነጋገርና በመመካከር መፍታት ይገባል" ሲሉ አስገንዝበዋል።

የጋራ የሆነችን ሀገር የምንጠብቀውና የምናስቀጥለው በመለያየት ሳይሆን በመተባበርና በመተጋገዝ በመሆኑ ወጣቶች ለአንድነት ዘብ ሊቆሙ ይገባዋል" ብለዋል።

ሙስሊም ምእመናንም የኢድ አልፈጥር በዓልን በመተጋገዝና በመተባበር እንዲሁም  የተቸገሩ ዜጎችን በማገዝ ሊያከብሩ እንደሚገባ ሃጅ ሸህ አህመድ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም