የጎንደር ከተማ የክርስትና እምነት ተከታዮች ነገ የሚከበረውን የኢድ አል ፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ በአዘዞ አቡበከር መስጅድ የጽዳት ስራ አከናወኑ

220

ሚያዚያ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጎንደር ከተማ የክርስትና እምነት ተከታዮች ነገ የሚከበረውን የኢድ አል ፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ በአዘዞ አቡበከር መስጅድ የጽዳት ስራ አከናወኑ።

በጽዳት መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙ ወጣቶች ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከቀናት በፊት ተከስቶ የነበረው ግጭት የሁለቱንም ሀይማኖት ተከታዮች የማይመጥንና የማይገልጻቸው መሆኑንም በተግባር አስመስክረዋል።

የጎንደር ከተማ የክርስትና እምነት ተከታዮችም በዓሉ የሚከበርበትን የአቡበከር መስጅድን በጋራ አጽድተዋል።

በጎንደር ከተማ የሚኖሩ የክርስትናና እስልምና እምነት ተከታዮች ፈተናዎችን በጋራ በማለፍ ዘመናትን የተሻገረ ቁርኝት ያላቸውና ለሌሎች አካባቢዎች የመቻቻል ተምሳሌት መሆናቸውንም የጽዳት ስራው ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

የበዓል ማክበሪያ ቦታዎችን ማጽዳት ለይስሙላ የሚከናወን ሳይሆን ዘመናትን የተሻገረ የጎንደር ህዝብ የመከባበር እሴት እንደሆነም አስገንዝበዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት በከተማዋ የተከሰተው ግጭት የሁለቱንም እምነት ተከታዮች የዳበረ አብሮነት የማይገልጽና የእኩይ ቡድኖች ተግባር ነው ብለዋል።

የእስልምና እምነት ተከታዮችም ከክርስትና እምነት ተከታዮች ጋር በትብብር በርካታ ማህበራዊ ጉዳዮችን እንደሚወጡ አመልክተዋል።

ከሰሞኑ በከተማዋ የተፈጠረው ግጭት የማንንም እምነት የማይወክል ለእኛም እንግዳ የሆነ ክስተት ነው ብለዋል።

1 ሺህ 443ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ነገ ይከበራል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም