በሃይማኖቶች መከካል ያሉ ልዩነቶች ለእኩይ ዓላማ ማስፈጸሚያ እንዳይውሉ ማስተማር ይገባል-ምክር ቤቱ

154

ባህር ዳር ሚያዝያ 23/2014 (ኢዜአ)  በሃይማኖቶች መካከል ያሉ ልዩነቶች ለእኩይ ዓላማ ማስፈጸሚያ እንዳይውሉ ምዕመናንን ማስተማርና መገሰጽ የሁሉም የሀይማኖት አባቶች ተግባር ሊሆን እንደሚገባ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አስገነዘበ።

የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼህ ሰይድ መሐመድ 1 ሺህ 443ኛ ኢድ አልፈጥር በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልክት አስተላልፈዋል።

ፕሬዚዳንቱ በዚህ ወቅት እንዳሉት በሃይማኖቶች መካከል ያሉትን ልዩነቶች ለጥፋት ተልዕኮ ማስፈጸሚያ ለማድረግ የሚሞክሩ ኃይሎችን መታገል ይገባል።

እነዚህ ኃይሎች በሃይማኖቶች መካከል ጣልቃ በመግባት ልዩነቶችን በማስፋት  ለጥፋት ዓላማቸው ስለሚያውሉት የሁሉም ሀይማኖት አባቶች ማስተማርና መገሰጽ እንደጠበቅባቸው ተናግረዋል።

የረመዳን ወር ህዝበ ሙስሊሙ በበጎ ተግባራት በመትጋትና በፆምና ፀሎት ያሳለፈው ወር መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ በጎና የመተዛዘን ተግባር ቀጣይነት ሊኖረውና የዘወትር ተግባር እንዲያደርገው አስገንዝበዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር ችግረኞችን በመርዳትና በመተሳሰብ እንዲያሳልፈው ሼህ ሰይድ አሳስበዋል።

“ከኢድ ሰላት በኋላ ጎረቤቶቹንና ቤተሰቦቹን በመዘየርና የተቸገሩትን በማብላትና በማጠጣት ማክበር ይገባል” ብለዋል።

እንዲሁም በዓሉ ለአገር ድህንነትና ለህዝቦች ደህንነት በመፀለይ እንዲከበር ፕሬዚዳንቱ ጠይቀዋል።

1 ሺህ 443ኛ ኢድ አልፈጥር በዓል ነገ ይከበራል።