በአንድ ቦታ በተከሰተ ግጭትን ሳቢያ የራስ አጀንዳን ለማስፈጸም የሚደረግ ሙከራ በጊዜ ሊቀጭ ይገባል

125

ጭሮ ሚያዝያ 23/2014 (ኢዜአ) በአንድ ቦታ በተከሰተ ግጭት የራስ አጀንዳ ማስፈጸሚያ ማድረግ በጊዜ ሊቀጭ ይገባል ሲሉ የምዕራብ ሐረርጌ ዞን የኃይማኖት አባቶች አስገነዘቡ ።

የኃይማኖት አባቶቹ ለኢዜአ እንደገለጹት በጎንደር ሰሞኑን ያጋጠመውን ያልተገባ ክስተት በመቃወም ሰበብ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ተቃውሞ የሚመስሉ ግን ግጭት የመፍጠር አዝማሚያ ያላቸው ሰልፎች በየቦታው ተስተዋሉ ነው።

“የቅዱስ ቁርዓን አስተምህሮ ክፉ ያደረገብህን በመልካም መልስለት” የሚል ነው ሲሉ የምዕራብ ሀረርጌ ዞን እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ መሐመድ አብዱራህማን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የየትኛውም እምነት ተከታይ ወንድሞች ላይ የደረሰን በደል የትም እና መቼም ቢሆን “በክፋት መመለስ አይፈቀድለትም” ብለዋል፡፡

በኃይማኖት ሽፋን የሀገርና ህዝብን ሰላም ለማደፍረስ ግጭቱን የፈጠሩ ጥፋተኞች ለህግ ቀርበው የሚገባቸውን ፍርድ እንዲያገኙ መጠየቅ ይጠበቅብናል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

የኦርቶዶክስ ኃይማኖት አባቶችም ከጎናችን ቆመው ጥፋተኞችን በመቃወምና ድርጊቱ በማውገዝ እንዲታረም እያደረጉት ያለውን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉም ሼህ መሀመድ ጠይቀዋል፡፡

በዞኑ የደብረ ፂዮን ቅድስት ልደታ ለማሪያም ቤተክርስቲያን ኃላፊ ሊቀ ምሁራን ክንፈ ርግብ ተሾመ በበኩላቸው የኢትዮጵያውያን ጠንካራ በአብሮነትና በአንድነት የተቆራኙ ሕዝቦች ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም በኃይማኖት ሽፋን ህዝብን በማጋጨት የራስ ድብቅ አጀንዳን ለማሳካት የሚደረግ ሙከራ ፈጽሞ እንደማይሳካ በአጽኖት ተናግረዋል፡፡

ቅዱስ ቁርዓንም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ “እርስ በርሳችሁ ተፋቀሩ ወንድሞቻችሁን እንደ ራሳችሁ ውደዱ የበደሏችሁንም ይቅር በሉ” የሚል አስተምህሮ ያለመሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ህዝቡ በሰከነ መንፈስ ነገሮችን በማጤን ጥፋቱ እንዳይበራክት በኃይማኖት ስም ወንድማማቾችን ለማጋጨት የሚደረገውን ድርጊት በፅኑ መቃወምና ማውገዝ እንዳለበት ሊቀ ምሁራን ክንፈ ርግብ አስገንዝበዋል፡፡