በጋሞ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በጋሞ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ

አርባ ምንጭ ሚያዝያ 23/2014 (ኢዜአ) በጋሞ ዞን በተለያዩ የልማት ዘርፎች ለመሰማራት ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠቱን የዞኑ ኢንቬስትመንት ማስፋፊያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በጽህፈት ቤቱ የመሬት አቅም ጥናት ፕሮሞሽን ሥራ ሂደት ባለሙያ ወይዘሮ ፍቅርተ ዘሪሁን እንደገለጹት የኢንቨስትመንት ፈቃዱ የተሰጠው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ነው።
ባለሀብቶቹ ፈቃዱ የተሰጠው በዞኑ በተለያዩ የልማት ዘርፎች ለመሰማራት ያቀረቧቸው 27 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ተቀባይነት በማግኘታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃዱን የወሰዱት በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በተለያዩ የአገልግሎት መስጫ ዘርፎች ለመሰማራት ነው ብለዋል።
ለባለሀብቶቹ በገጠር ወደ 600 ሄክታር የሚጠጋ በከተሞች ደግሞ 14ሺህ 950 ካሬ ሜትር መሬት በመስጠት መሬት መሰጠቱን ወይዘሮ ፍቅርተ ተናግረዋል።
ባለሙያዋ እንዳሉት አብዛኞቹ ባለሀብቶች የግንባታ ሥራ የጀመሩ ሲሆን ቀሪዎቹ ዝግጅት ላይ ናቸው።
ባለሀብቶቹ ግንባታቸውን አጠናቀው በሙሉ አቅማቸው ምርትና አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩም ለ12 ሺህ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩም አስታውቀዋል።
የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ ከገቡት ፕሮጀክቶች መካከል “የኢንጂነር ካሣሁን አስራት ጥምር ግብርና ድርጅት” አንዱ ነው።
የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሻገር አስራት እንዳሉት ድርጅቱ በ17 ሚሊዮን ብር ካፒታል በዞኑ ዳራማሎ ወረዳ በዘመናዊ የእንስሳትና ሰብል ልማት ለመሰማራት 137 ሄክታር መሬት ተረክቧል።
ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ከተረከበው መሬት ውስጥ በ120 ሄክታር መሬት ላይ በዘመናዊ መስኖ ማሾ፣ በቆሎና አቦካዶ ማልማት መጀመሩን ተናግረዋል።
በቀሪው መሬት ላይ ደግሞ የእንስሳት እርባታ ለማካሄድ የሚያስችለውን ግንባታ እያከናወነ እንደሚገኝ መሆኑን አስረድተዋል።
እንደ ሥራአስኪያጁ ገለፃ ድርጅቱ እስካሁን ባደረገው እንቅስቃሴ ለ153 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል።