በደራሼ ልዩ ወረዳና አካባቢው አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የተቀናጀ ስራ እየተሰራ ነው

158

ሚያዚያ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) በደራሼ ልዩ ወረዳና አካባቢው አስተማማኝ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የተቀናጀ ስራ እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እና የሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቁ።

የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እና የሰላምና ፀጥታ ቢሮ በደራሼና አካባቢው ያለውን ወቅታዊ ጉዳይ አስመልክተው ትናንት ማምሻውን አርባ ምንጭ ላይ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም በደራሼና አካባቢው ሰሞኑን ማህበረሰቡን የማይወክል አስነዋሪ ድርጊት በጥቂት ፅንፈኛ የጥፋት ቡድኖች መፈጸሙን ገልጸዋል።

ፅንፈኛ የጥፋት ቡድኖቹ በፈጸሙት አስነዋሪ ድርጊት ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱን ኮሚሽነሩ እና የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊው በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዓለማየሁ ማሞ ከሚያዝያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በደራሼ ልዩ ወረዳ ፀረ-ሰላም ቡድኖች በሸረቡት ሴራ የፀጥታ ችግር መከሰቱን ገልጸዋል።

እንደ ኮሚሽነር ዓለማየሁ መግለጫ፤ ፅንፈኛ የጥፋት ቡድኖቹ በፈጸሙት አረመኔያዊ ድርጊት በፀጥታ አካላትና በአካባቢው አመራሮች ከፍተኛ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ተፈጽመዋል፤  የህዝብ ሀብት ንብረት ወድሟል፤ ተዘርፏል።

የክልሉ ልዩ ኃይል፣ የፈዴራል ፖሊስና መከላከያ ሠራዊት ከህዝቡ ጋር በመሆን በአካባቢው ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአካባቢው በተፈጸመው የወንጀል ድርጊት እጃቸው ያለበት አካላትን ለይቶ በቁጥጥር ስር ለማዋል ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

ለስራ ስኬታማነት የአካባቢው ኅብረተሰብ፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የባህል መሪዎች ከመንግሥት ጋር በመተባበር ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ እያደረጉት ያለውን ሁሉን አቀፍ ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ኮሚሽነር ዓለማየሁ ጠይቀዋል።

የደቡብ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ባውዲ በበኩላቸው ሚያዝያ 17 ቀን 2014 ዓ.ም በአካባቢው በተለምዶ ሆልቴ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በሕንድ ዜጎች ላይ እገታ መፈጸሙን ተከትሎ የክልሉና የፈደራል ፀጥታ ኃይሎች ወደቦታው መንቀሳቀሳቸውን ገልጸዋል፡፡

ኃላፊው በመግለጫቸው እንዳሉት፤ ፅንፈኛው የጥፋት ቡድን በተደራጀ መንገድ ታጥቆ በወረዳ አመራሮችና በፀጥታ ኃይሎች ላይ እጅግ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ፈጽሟል፤ መኖሪያ ቤቶችን አቃጥሏል፤ ሀብት ንብረት አውድሟል፤ ዘርፏል።

አጥፊ ቡድኑ የፈጸመው ድርጊት የደራሼ ልዩ ወረዳ ህዝብንም የማይወክል፣ ከኢትዮጵያዊ  ማንነት ያፈነገጠ እጅግ አረመኔያዊ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አካባቢውን በማረጋጋት ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር፣ የህግ የበላይነትን ለማስከበር፣ ክልሉ በተደራጀ መንገድ ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ አቅርቦ አካባቢው እስኪረጋጋ ድረስ በፀጥታ ኃይሉ ዕዝ ስር እንዲሆን መደረጉን  ኃላፊው በመግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊትም ከክልሉ መንግሥት ጋር በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ አካባቢውን የማረጋጋትና የወንጀል ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትን በመለየት ከሕዝብ ጋር ሆኖ ለህግ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የደራሼ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

በየአከባቢው በተፈጠሩ ችግሮች እጃቸው ያለበትን አካላትና የደረሰውን የጉዳት መጠን ዝርዝር መረጃ የማሰባሰብ ስራ እየተሰራ ሲሆን፤ ሲጠናቀቅ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያየ መልክ ያለው የፀጥታ ችግር ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችን ለመቆጣጠር እየተደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ርብርብ ስኬት ህዝቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም