ርእሰ መስተዳድሩ ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወር አጉልቶ ያሳየውን የመረዳዳት እሴት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቀረቡ

112

ሀዋሳ ሚያዝያ 23/2014 (ኢዜአ)ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወር አጉልቶ ያሳየውን የመረዳዳትና የመደጋገፍ መልካም እሴት በቀሪ ጊዜያትም አጠናክሮ እንዲቀጥል የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ጥሪ አቀረቡ።

ርዕሰ መስተዳድሩ 1443ኛውን የኢድ አል ፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ  ዛሬ ባስተላለፉት  የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት  ህዝበ ሙስሊሙ በቅዱሱ የረመዳን ወር ለሀገራችን ሰላምና ለህዝቦች አንድነት በጾምና በጸሎት ሌት ተቀን ሲተጋ ቆይቷል።

የኢድ አል ፈጥር በዓል የእዝነትና የርህራሄ፣ የመተሳሰብ፣ ያለው ለሌው በማካፈል በአብሮነት የሚያሳልፈው እና ማህበራዊ ግንኙነትን የበለጠ የሚያጠናከርበት በመሆኑ በተለይ በዚህ የችግር ወቅት ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን በመደጋገፍ እና በመረዳዳት ሊያሳልፈው እንደሚገባ አመልክተዋል።

“በተለይ በአሁኑ ሰዓት በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋ ለችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን መደገፍ ከሁሉም ይጠበቃል” ብለዋል።

በዚህ ረገድ ሙስሊም በነፍስ ወክፍ የሚያወጣውን “የዘካተል ፍጥር” የእህል ስጦታ በማስተባበር በብዙ መልኩ ችግር ውስጥ ላሉ ሰዎች በማበርከት የወገን አለኝታነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል ርእሰ መስተዳደሩ አክለው እንዳሉት አሁን ላይ ሀገራችን እንዳትረጋጋ የሚሹ ሀይሎች አንዴ የብሔር ገጽታ በሌላ ጊዜ ደግሞ የሀይማኖት ሽፋን በመስጠት ህብረተሰቡን እያሸበሩ ይገኛሉ።

“ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እያስተናገደች የገጠሟትን ፈተናዎች ደግሞ በህዝቦቿ ብርቱ ጥረት በጽናት እየተሻገረች ላለችው ሀገራችን የሰላም እጦት ሲጨመር እድገታችንን ወደ ኋላ መጎተቱ አይቀርም” ሲሉ ተናግረዋል።

“በዚህ ደግሞ ተጎጂ የምንሆነው ሁላችንም ነን እንጂ ጥቂቶች ብቻ አይደሉም” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ሰላም የሰፈነባትና የበለፀገች ሀገር ለመጪው ትውልድ ማስረከብ የሁሉም ኀላፊነት ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።

“በተለይም ደግሞ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተምሳሌት ሆነው ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ሀገር አንድነት ሊያስተምሩና ሊመክሩ ይገባል” ሱሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሰሞኑን ለዘመናት ተቻችለውና ተከባብረው በኖሩ የእስልምና እና የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ቅራኔ እንዲፈጠር የሚሹ አካላት የነሱን ጉዳይ አስፈጻሚዎች በመጠቀም በሀይማኖት ተቋማት ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ምክንያት መሆናቸውን አስታውሰዋል።

እንደ አቶ ርስቱ ገለፃ በክልላችንም ሆነ በሀገራችን እየተስተዋለ ያለው ጽንፈኝነት ከእምነቶች አስተምህሮት ባፈነገጠ መልኩ የግል ፍላጎት እና የፖለቲካ ትርፍ ማካበት በሚፈልጉ አካላት የሚፈጸም እንደሆነ እሙን ነው።

ህዝበ ሙስሊሙም ሆነ የሌላው እምነት ተከታይ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የጽንፈኝነት እንቅስቃሴዎችን የከፋ አደጋና ጉዳት እንዳያደርስ ካላከሸፈ የመጀመሪያ ተጎጂው ራሱ በመሆኑ ከወዲሁ አምርሮ በተደራጀ መልኩ  እንዲታገል አሳስበዋል።

መላው የክልሉ ህዝብ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ እንዲሁም ለዘመናት የገነባነውን የሰላም፣የመቻቻል፣የአብሮነት፣ የመከባበር እና የመደጋገፍ እሴት በማጠናከር ሀገራዊ የለውጥ ጉዞውን እንዲያሳካ አቶ ርስቱ ምልእክት አስተላልፈዋል።

ርእሰ መስተዳደሩ ለመላው የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች የኢድ አልፈጥር በዓል የሰላምና የአብሮነት እንዲሆን ተመኝተዋል።