በመዲናዋ የኢድ ሶላት ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶች ይፋ ሆኑ

112

ሚያዝያ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) 1 ሺህ 443ኛው የኢድ አልፈጥር ረመዳን በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታና የደህንነት የጋራ ግብረ ሐይል አሰፈላጊውን ዝግጀት አጠናቆ ወደሥራ መግባቱን አስታወቀ፡፡

በየዓመቱ ለሚከበረው የኢድ አልፈጥር የረመዳን በዓል ወቅታዊውን የፀጥታ ሁኔታ ያገናዘበ ዕቅድ በማውጣት እና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በዓሉ በሠላም እንዲከበር የፀጥታና የደህንነት የጋራ ግብረ ሐይል አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የዘንድሮው የኢድ አልፈጥር ረመዳን በዓል አከባበር አገራችን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ልዩ ዝግጅት ከመደረጉም ባሻገር ከእምነቱ አባቶችና ከወጣት በጎ ፈቃደኞች ጋር በበዓሉ አከባበር ዙሪያ አስቀድሞ ተገቢውን ውይይት በማድረግ ዝግጅት መደረጉ ነው የተገለጸው፡፡

የበዓሉ ታዳሚዎች በየአካባቢያቸው በዓሉን ሲያከብሩም ሆነ ወደ ኢድ ሶላቱ ሲመጡ እንደወትሮው ሁሉ የፖሊስን መስተንግዶና ትዕዛዝ በማክበር ተባባሪ እንዲሆኑ የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

የፀጥታና የደህንነት የጋራ ግብረ ሐይል 1443ኛው የኢድ አልፈጥር ረመዳን በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የሚያከናውነውን ተግባር በመደገፍ የከተማችን ነዋሪዎች የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙም በአዲስ አበባ ፖሊስ የመረጃ ስልኮች 011-1 11-01-11 ወይም በነፃ የስልክ መስመር 991 መረጃ መስጠት እንደሚቻል ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በተያያዘ ዜና ነገ ሚያዚያ 24 ቀን 2014 ዓ.ም ዓ.ም የኢድ ሶላት ተጀምሮ እሰከሚጠናቀቀ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶች ይፋ ተደርገዋል፡፡

የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር አሽከርካሪዎች ከዚህ በታች የተገለፁት መንገዶች ዝግ መሆናቸውን ተገንዝበው ሌሎች አማራጮችን እንዲጠቀሙ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል፡፡

በዚህም መሰረት፡-- ከቦሌ አየር መንገድ በሚሊኒየም አዳራሽ ወደ ስታዲዩም የሚወስደው መንገድ ደንበል ሲቲ ሴንተር ኦሎምፒያ አደባባይ አከባቢ- ከመገናኛ ፣ በሃያ ሁለት ወደ መስቀል አደባባይ እንዲሁም ከቦሌ መድሃኒያለም፣ በአትላስ ሆቴል ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ኡራኤል ቤተ-ክርስቲያን አካባቢ- ከአራት ኪሎ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ባሻ ወልዴ ችሎት ወይም ፓርላማ መብራት-

ከፒያሣ አካባቢ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ቸርችር ጎዳና ቴዎድሮስ አደባባይ- ከተክለ ሀይማኖት በሜትሮሎጂ ወደ ስታዲየም የሚወስደው መንገድ ሜትሮሎጂ መስሪያ ቤት አካባቢ- ከተክለ ሀይማኖት ፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሚወስደው መንገድ ጥቁር አንበሳ የኋላ በር አካባቢ- ከሲኒማ ራስ በጎላ ሚካኤል ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ጎላ ሚካኤል መስቀኛ- ከጌጃ ሰፈር ፣ ጤና ጥበቃ፣ ብሄራዊ ቲያትር የሚወስደው መንገድ

ጎማ ቁጠባ- ከባሻ ወልዴ ችሎት በኦርማ ጋራዥ ወደ ፍል ውኋ መስኪድ የሚወስደው መንገድ ንግድ ማተሚያ ቤት - ከጎፋ በቅዱስ ቂርቆስ ቤ/ክ ወደ ለገሐር አዲሱ መንገድ የሚወስደው መንገድ ቅዱስ ቂርቆስ ቤ/ክ መስቀለኛው ላይ- ከጦር ኃይሎች ፣ ልደታ ፣ ፖሊስ ሆስፒታል ሜክሲኮ አደባባይ - ከሳሪስ በጎተራ ወደ መስቀል አደባባይ የቀድሞ አራተኛ ክፍለ ጦር አካባቢ መንገዱ የሚዘጋ ሲሆን ይለፍ ለሌላቸው ተሽከርካሪዎች ከለሊቱ 10፤00 ሰዓት ጀምሮ ዝግጅቱ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ዝግ ይሆናል ፡፡

በተጨማሪም ከሳሪስ እና ከጎተራ ወደ አዲስ አበባ ስታዲዩም ለሚመጡ ከባድ ተሸከርካሪዎች መንገዱ አጎና ሲኒማ ጋር የሚዘጋ ይሆናል፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ ከፖሊስ የተሰጠውን መረጃ ተገንዝቦ የትራፊክ ፖሊስ አባላት በሚጠቁሙት አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀም እና ለትራፊክ ፖሊስ አባላት ትዕዛዝ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪው አቅርቧል፡፡ለእምነቱ ተከታዮች በዓሉ የፍቅር የሰላም እንዲሆን የፀጥታና የደህንነት የጋራ ግብረ ሐይል መልካም ምኞቱን ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም