ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዘላቂ የተቋም ግንባታን ለማረጋገጥ የጀመረውን የለውጥ ስራ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል-ምክር ቤቱ

199

ሚያዚያ 22/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዘላቂ የተቋም ግንባታ ለማረጋገጥ እያከናወነ ያለውን የለውጥ ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስገነዘበ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቦርዱን የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ ሂደት ዋና ዋና ሁነቶችን ሪፖርት አቅርበዋል።

በሪፖርታቸውም ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም እና መስከረም 20 ቀን 2014 ቀን የተካሄዱ ምርጫዎች ሂደት አጠቃላይ አፈጻጸምን በዝርዝር አቅርበዋል።

ቦርዱ በምርጫው የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በመገምገም የተገኙ ትምህርቶች እና በቀጣይ መሻሻል ያለባቸው ነጥቦች ላይ ጥናት በማስጠናት ምክረ ሃሳብ እንደቀረበለትም ገልጸዋል፡፡

የምርጫ ጣቢያዎችን ማቋቋም ፣ የምርጫ አስፈጻሚ ሰራተኞች ምልመላና ስልጠናና የድምጽ አሰጣጥና ቆጠራ በጥናቱ ምክረ ሃሳብ ከቀረበባቸው ውሰጥ ናቸው።

ኢትዮጵያ ዘላቂና ጠንካራና ምርጫ አስፈጻሚ ተቋም እንዲኖራት በቴክኖሎጂ የታገዙ የለውጥ ተግባራትን ቦርዱ እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የዴሞክራሲ ተቋማት ነጻና ገለልተኛ ሆነው በመቋቋማቸው በኢትዮጵያ ምርጫ ታሪክ የ6ኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊና በህዝብ ዘንድ ተአማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ ማድረጉንም ነው ቋሚ ኮሚቴው ያነሳው ፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በጸጥታ ችግር ምክንያት ምርጫ ባልተካሄደባቸው አከባቢዎች ምርጫ ለማካሄድና የፖለቲካ ፓርቲዎች ህግና ስርአትን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ረገድ ቦርዱ እያከናወነ ያለውን ተግባር ጠይቀዋል።

የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ቦርዱ በጸጥታ ምክንያት ምርጫ ያልተካሄደባቸው አካባቢዎችን በዘንድሮው  በጀት ዓመት ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑን በምላሻቸው አመላክተዋል።

በአማራ፣ አፋር፣ ደቡብ፣ ኦሮሚያ ክልል ምርጫ የሚደረግባቸውና የሚደገምባቸው የተወሰኑ ቦታዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤  ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በጸጥታ ምክንያት በበርካታ አካባቢዎች ምርጫ አለመደረጉን  ገልጸዋል።

በመሆኑም ቦርዱ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ ማዕከል በማድረግ የቀሩ ምርጫዎችን ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከህግና ስርአት ውጪ የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች በማስረጃ ላይ በመመስረት እንዲያስተካክሉ ቦርዱ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

የህግ፣ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እጸገነት መንግስቱ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዘላቂ የተቋም ግንባታ ለማረጋገጥ እያከናወነ ያለውን የለውጥ ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

ቦርዱ በተወሰኑ ምርጫ ክልሎች የቀረቡ አቤቱታዎች የታዩበትና ቅሬታዎች የተፈቱበት መንገድ እንዲሁም ሌሎች ቦርዱ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ላይም ማብራሪያ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም