ወጣቶች በሃይማኖት ሽፋን ግጭት በመቀስቀስ አገርን ለማተራመስ የሚንቀሳቀሱ አካላት መጠቀሚያ መሆን የለባቸውም

88

ሚያዚያ 22/2014/ኢዜአ/ ወጣቶች በሃይማኖት ሽፋን ግጭት በመቀስቀስ አገርን ለማተራመስ የሚንቀሳቀሱ አካላት መጠቀሚያ መሆን እንደሌለባቸው ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ወጣቶች ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ ለማፍረስ የሚሹ አካላት የጥፋት ሴራ በመሸረብ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ቢሆንም እኩይ ሃሳባቸው መቼም ቢሆን አይሳካም ብለዋል፡፡  

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ወጣቶች "ወጣቱ ትውልድ የታሪካዊ ጠላቶች ፍላጎት መጠቀሚያ መሆን የለበትም" ብለዋል፡፡  

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የሃይማኖት መቻቻልና መከባበር ያለባት አገር መሆኗንም ጠቅሰው፣ ሴረኞች ሁከት ለመፍጠር በተለያዩ ነገሮች ሞክረው ሳይሳካላቸው ሲቀር ህዝቡን በሃይማኖት ለማጋጨት መነሳታቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህ እኩይ ድርጊት እንዲከሽፍና ኢትዮጵያዊያን እንደቀደመው አብረው እንዲኖሩ ለማድረግም ወጣቶች ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለሚሹ አካላት መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ሊጠነቀቁ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡

ወጣቶች  ከስሜታዊነት በጸዳ መልኩ፣ አሉባልታ ወሬዎችን ባለመስማት እና ህዝቡን በሃይማኖት ለማጋጨት የሚሹ አካላትን ባለመተባበር ሊያጋልጧቸው ይገባል ብለዋል፡፡  

ኢትዮጵያ ወደ ልማት ፊቷን እንዳታዞር የሚሹ አካላት የተለያዩ አጀንዳዎችን በመፍጠር ህዝብን ለማጋጨት እየሰሩ ነው፤ ነገር ግን ይህ ተግባር ፈጽሞ አይሳካም ነው ያሉት፡፡

ወጣቶች  በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መረጃዎችን ትክክለኝነት መመርመር እንዳለባቸውም  ነው የገለጹት፡፡  

ኢትዮጵያዊ አንድነትን፣ መተባበርና መከባበርን በማጎልበት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ማለፍ እንደሚገባም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡  

በተለያዩ አካባቢዎች ግጭት በመፍጠር ለዘመናት አብሮ የኖረውን ህዝብ በሃይማኖት ለማጋጨት እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ አካላትን መንግስት ከህዝቡ ጋር በመተባበር በቁጥጥር ስር እያዋለ እንደሚገኝ መግለጹ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም