የአዋሽ ተፋሰስ የጎርፍ አደጋ ስጋትን ለመከላከል የሚያስችል ልዩ ግብረ ሃይል ተቋቋመ

42
አዲስ አበባ  ጳጉሜን 2/2010 የአዋሽ ወንዘ ተፋሰሶችን የጎርፍ አደጋ ስጋት ለመከላከል የሚያስችል ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተውጣጣ ልዩ ግብረ ሃይል መቋቋሙ ተገለጸ። የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ  በቀጣዮቹ ቀናት የዝናቡ መጠን በብዙ የአገሪቱ አካባቢ እየቀነሰ ቢመጣም በአዋሽ ተፋሰስና በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍና የወንዝ ውሃ ሙላት የመከሰት እድሉ ሰፊ መሆኑን ተንብይዋል። የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ እንዳሉት፤ በአካባቢው የጎርፍ አደጋ ቢከሰት አስቀድሞ ጥንቃቄ ለማድረግ፣ አስፈላጊውን ምላሽ ለመስጠትና የመልሶ ማቋቋም ስራ ለመስራት ልዩ ግብረ ሃይል ተቋቁሟል። ግብረ ሃይሉ ከአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን፣ የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር፣ የኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን፣ ከስኳር ኮርፖሬሽን፣ ከብሔራዊ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን፣ ከኦሮሚያና ከአፋር ክልል የሚመለከታቸው አካላት የተውጣጣ ነው። በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚመራው የመደበኛ የጎርፍ አደጋ ስጋት ምክር ቤት በተለየ ሁኔታ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ትዕዛዝ ግብረ ሃይሉ ለአጭር የስራ ጊዜ ተቋቁሟል። የጎርፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው አካባቢዎች በላይኛው አዋሽ ተፋሰስ በኢሉ፣ በቾ፣ ሰበታ፣ ኤጄሬ፣ በመካካለኛው አዋሽ ቦራ፣ ወንጂ፣ ቦሰትና ፈንታሌ፣ በታችኛው አዋሽ አፋር፣ ዱብቲ፣ አሳይታና ሚሌ፣ ገዋኔ፣ ቡሬሙዳይቱ፣ አሚባራና አዋሽ ፈንታሌ ተጠቃሾች ናቸው። ግብረ ሃይሉ በእነዚህ አካባቢዎች በወንዝ ሙላት ሳቢያ የሚከሰት የጎርፍ አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር ለመስራት የቅድመ ዝግጅት ስራ ጀምሯል። የአዋሽ ወንዝን ጉዳት በዘላቂነት ለመፍታትና አደጋ የሚያስከትለውን ውሃ ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት የአዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ግዛው ናቸው። የአዋሽ ለአካባቢው በተለይ የከሰም ወንዝ በየዓመቱ እየሞላ ለህብረተሰብ ስጋት ሆኖ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ወንዞቹ ወደ ልማት ለመለወጥ እየተጠና ያለውን ጥናት ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል። የተቋቋመው ግብረ ሃይል እስከ መስከረም አጋማሽ ድረስ ይቆያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም