የምግብ ሉአላዊነት

157

አለም ቀጣዩ ምናልባትም ለረጅም ጊዜ የሚዘልቀውና ለቁጥጥር የሚያስቸግረው የሁሉም ሃገራት የብሄራዊ ደህንነትና የሉአላዊነት ስጋት ረሃብ ይሆናል በማለት መጨነቅና መብሰልለሰል የጀመረችው ከ28 አመታት በፊት በጣሊያኗ መዲና ሮም የተደረገውን ውይይት ተከትሎ መሆኑ ይነገራል።

Rome Declaration and Plan of Action በሚል መሪቃል ምግብን ለተመለከተ ጉባኤ የተቀመጡት የአለም መሪዎች ሁኔታዎች በወቅቱ በነበሩበት አካሄድ ከቀጠሉ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ይወጡና የአለም ሰላምና መረጋጋትም አደጋ ውስጥ እንደሚወድቅ በመረዳታቸው ረሃብ የሃገራት ብሄራዊ አደጋ ስጋት መነሻም መድረሻም ሊሆን እንደሚችል መገንዘባቸውን ይፋ አደረጉ።

ሁሉም ሰዎች በሁሉም ቦታ በቂ ጤናማ የተመጣጠነ ፍትሃዊ የምግብ አቅርቦት እንዲኖራቸውና የተረጋጋ ህይወት እንዲኖሩ ማድረግ ካልተቻለና ረሃብ የምግብ እጥረትና ያለመመጣጠን እንዲሁም የምግብ ዋጋ መወደድ የሚከሰት ከሆነ ችግሮች መልካቸውን በመቀያየር እየሰፉና እየከፉ ይመጣሉ ሲሉም አስጠንቅቀው ነበር።  

የምግብ ዋስትና ማጣት ብዙ መልኮች፣ መንስኤዎችና ውጤቶችን በመያዝ የአለም ህዝብ ላይ ሲከሰት፣ ችግሮቹ በአለም፣በአህጉር፣በሃገር፣በአስተዳደር ክልሎች፣በማህበረሰብና በቤተሰብ አልፎም እስከ ግለሰብ የዘለቁ ምስቅልቅሎችን በማስከተል በተለይም በህሙማን፣በሴቶች፣በህጻናት፣በአረጋውያንና በአካል ጉዳተኞች ላይ ችግሩን ስለሚያበረታ መፍትሄ እንዲፈለግ በማሰብ በምእተ አመቱ የልማት ግቦች (MDGs), ውስጥ በልዩ ትኩረት እንዲካተተ ተደርጎ እንደነበር ስለጉዳዩ የተጻፉ ሰነዶች ያስረዳሉ።

በፈረንጆቹ 2015 እንዲጠናቀቁ ታላሚ ተደርገው የነበሩት የምእተአመቱ የልማት ግቦች በተለያዩ ምክንያቶች ሊሳኩ ባለመቻላቸው ዘላቂ የልማት ግቦች (SDGs) በሚል ተተክተው እንቅስቃሴዎች ቢደረጉም ውጤታማነታቸው በቅጡ እንኳን ሳይፈተሽ አለማችን ከኮቪድ 19 ጋር በመተናነቅ እንደጀመረች ይታወሳል።

አለም ውላ የምታድርባቸው ሁኔታዎች በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነ የሚላስ የሚቀመስ እንደማይኖር ሊታወቅ ይገባል የሚሉት የፓኪስታን የዘላቂ የልማት ግቦች ፖሊሲ ተቋም ዋና ዳይሬክተር አብዲቃዩም ሱሌሪ “ያለንበት ወቅት ሃገራት ያለባቸውን የዜጎች የምግብ ፍላጎትና ጥያቄ ክፍተት መሙላት እርስ በእርስ ተሳስረው የባህልና የተሞክሮ ልውውጥ ሊያደርጉበት የሚገባ ነው” ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ የምግብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ ካስፈለገ ምግቡን በብዛትና በጥራት የሚያመርቱ ሰዎች እርሻ እንዲያርሱ የሚያስችሉ የጸጥታ ዋስትና፣ማዳበሪያና ሌሎች ግብአቶች፣ሙያዊ ድጋፍ፣አነስተኛ ወለድ ያላቸው የብድር አማራጮች እንዲሁም ስለምርታቸው የገበያ ዋጋ የውሳኔ ነጻነትን የመሳሰሉ ምቹ መደላድሎች ሊፈጠርላቸው የሚገባ ከመሆኑም ባለፈ ሃገራት ከተማ ነክ ፖሊሲዎቻቸው ላይ የሰጡትን ልዩ ትኩረት ወደ ገጠሩም ቢያደርጉት ከከተማ ነዋሪ መጨመርና ተያያዥ ችግሮችን በመቀነስ በብዙ ያተርፋሉ ብለዋል።

ከእርሻ የሚገኘው የምግብ ምርት ብቻውን የሚፈለገውን ያህል የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የብሄራዊ ደህንነት ስጋትነቱን ይቀንሳል ማለት እንዳልሆነ ያሰመሩበት ዳይሬክተሩ ከምግብ ምርትና ዝግጅት ጋር የተያያዙ ግብአቶች ማለትም ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣የተመጣጠነ የእንስሳት መኖ፣የሰዎችና የእንስሳት ንጽህናና ጤንነት፣የሃይል ተደራሽነትና የተመጣጠነና ጤናማ የምግብ አዘገጃጀት ስልጠናዎችን የመሳሰሉ ጉዳዮች ትኩረት እንዲያገኙና ይመለከታቸዋል የሚባሉ አካላት ሁሉ ሲሰሩባቸው እንደሚገባም ገልጸዋል።

ሁሉንም የግቡን ማጠንጠኛ የሆነውን የምግብ ጉዳይ ቸለል በማለት የተቀሩት ግቦች ይሳካሉ ማለተ እንደማይቻል የሚያብራሩት የምግብ ዋስትናን የተመለከቱ ሰነዶች የብሄራዊ ደህንነት ስጋት የሆነውን የምግብ አቅርቦት ችግር በአስቸኳይ እርዳታ፣በገንዘበ እገዛ፣ በምግብ ልገሳና በመንግስት የምግብ አቅርቦት ጣልቃገብነት መፍታት ይቻለላል ማለት ችግሩ ስር እንዲሰድና የእርዳታ ጠባቂነት አመለካከት እንዲነግስ ብሎም ፍልሰትና ሌሎች ፖለቲካዊ ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ከማድረግ በዘለላ መፍትሄ ሊያመጣ እንደማይችል የተለያዩ ሃገራት ተሞክሮዎችን በማንሳት ይሞግታሉ።

ቸነፈር፣ረሃብ፣የምግብ እጥረት፣የምግብ ዋስትና ማጣት የመሳሰሉት ክስተቶች ከአንደኛው ወደ ሌላኛው እየተቀያየሩ ለበርካታ አስርት አመታት ትርፍ አምራች ናቸው ከሚባሉት ፓኪስታን ህንድና የላቲን አሜሪካ ታዳጊ ሃገራት ጋር ስለመዝለቃቸው የሚያትቱት እነዚህ ሰነዶች በፈረንጆቹ 2010 በፓኪስታን የመግዛት አቀም በማሽቆልቆሉ የተነሳ በትርፍነት የተቀመጠውን የስንዴ ምርት የሚገዛው የህብረተሰብ ክፍል በ10 በመቶ መውረዱን አስታውሷል።

በምግብ ዙሪያ እየሰሩ ያሉ በርካታ ድርጅቶች ከሚያነሷቸው ሃሳቦች መካከል ዋነኛው ምግብን በተመለከተ የተራራቀውን የሰዎች አመለካከት መቀየርና ወቅቱን መሰረት ያደረጉ የአመጋገብ ስርአቶችን ይበልጥ ማስተዋወቅ የሚጠቀሱ ሲሆን ስንዴ፣ሩዝ፣በቆሎና ማሽላ ላይ ብቻ ትኩረት ያደረጉ የአመጋገብ ባህሎች በሃገራት መሪዎችና በሚመለከታቸው አካላት ብሎም የዜጎች ጥረት ሊስተካከሉ ካልተቻሉ ሃገራት ወደ ሚፈሩት የዜጎች አለመረጋጋትና የእርስበእርስ ጦርነት መግባታቸው አይቀሬ ነው።

የምግብ ምርቶች ላይ የሚታዩት ውስብስብ የገበያ ስርአቶች በጊዜው እየተፈተሹ መፍትሄ ሊበጅላቸው ካልቻለም የዜጎችና የአምራቾችን የመግዛትና የማምረት አቅም በመጉዳት የዋጋ ንረቶችን በማባባስ ችግሮቹ ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ ያደርጉታል በማለት የሚሞግቱት የግብርና ምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ህገወጥ የእንስሳትና የእህል ግብይቶች በተለያዩ የአለም ሃገራት በስፋት እየተስተዋሉ መምጣታቸውን ለዚህ ችግር ማሳያ መሆኑን ያሰምሩበታል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር የሚታተመው የአፍሪካን ሪኒዋል ድረገጽ እ.ኤ.አ ከ2007 እስከ 2019 ድረስ ባሉት አመታት የአፍሪካ የስንዴ ግዢ ፍላጎት በ68 በመቶ መጨመሩን ገልጾ አሁን ላይ ከ47 ሚሊየን ቶን በላይ የሱፍ ዘይትና ስንዴ ወደ አህጉሪቱ እንደሚላክ ባሳወቀበት ጽሁፉ በተነጻጻሪ ሰፊ የእርሻ መሬትና ብዙ የህዝብ ብዛት ያላቸው አልጄሪያ፣ግብጽ፣ናይጄሪያ፣ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ያሉ ዘጠኝ ሃገራት 80 በመቶ የሚሆነውን የስንዴ ፍላጎት ከሩሲያና ከዩክሬን እንደሚያሟሉ እወቁት ብሏል።

ሩሲያ ላይ የተጣለውን ሁሉን አቀፍ ማእቀብ ተከትሎ የሩሲያ መንግስት ምንም አይነት የግብርና ምርቶችን እና ለማዳበሪያ ምርት የሚሆኑ ግብአቶችን ላለመላክ ውሳኔ ላይ መድረሱና ዩክሬናውያን አምራቾችም በጦርነቱ ምክንያት እያመረቱ አለመሆኑ የምግብ እጥረቱን እንደሚያባብሰው ትንበያውን ያስቀመጠው ዘ ኮንቨርዜሽን ድረገጽም ጦርነቱ ሊገመት ባለመቻሉ የተፈጠረው የነዳጀ እጥረት የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ግብርናና የምግብ ዋጋ ንረት ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽእኖ እያሳረፈ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም ሲል አስነብቧል።

የተወሰነው የአለም ክፍል የሚፈልገውን አማርጦ እየተመገበ ሌላኛው በተራዘመ ረሃብ ውስጥ መኖሩ የተረጋጋ የአለም ሰላም እንደማያመጣ እየታወቀ ስለመምጣቱ አጽንኦት በመስጠት ሃሳባቸውን ለፎሬይንፖሊሲ ድረገጽ የላኩ የምግብ ጉዳዮች ምሁራን ሃገራትና ትልልቅ ኩባንያዎች በእርሻ ስራ ላይ ያልተሰማሩ ዜጎችን የመግዛት አቅም ለማሻሻል መጣር፣ለስራ አጦች የስራ እድል የሚፈጠሩበትን እድሎች ማስፋት ብሎም የጥገኝነት መጠንን ለመቀነስ የሚያስችሉ የፖሊሲ ሃሳቦችን አውጥተው ሊተገብሩ ይገባል ብለው ነበር።

እነዚህን እና ሌሎች ከምግብ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት እንኳን ባይቻል ሊቀንሱ የሚችሉባቸውን መፍትሄዎች የሚያመላክቱ አካላት ካቀረቧቸው አማራጮች መካከል የእርሻ ምርትን ማሳደግ፣ማሰባጠርና የአለም ማህበረሰብን ማቀራረብ ብሎም እንቅፋቶችን ማስወገድ በዋናነትየሚጠቀሱ ሲሆን ምግብን የተመለከቱ የአስተሳሰብና የተግባር መዛነፎች በተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ማስተካከል የሚለውም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

እንደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካባቢ ፕሮግራም ድረገጽ ሃተታ ከሆነ መቆሚያ ከሌለው የምግብ ዋጋ ንረት ባልተናነሰም በግርድፍ ግምት ከሲሶ በላይ የሚሆነው የአለማችን የምግብ ምርት እየባከነ ሲሆን በአውሮፓ በአውስትራሊያና በአሜሪካ ያሉ ግዙፍ ሱፐርማርኬቶች የሚያባክናቸውና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው አልፏል በሚል የሚያስወግዷቸው የእንስሳት ተዋጽኦ፣የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የሰብል ምርቶች ፍትሃዊና ተደራሽ ባልሆኑ የገበያ ስርአቶች ምክንያት እንዲወገዱ እንደሚደረጉ ገልጿል።

በአፍሪካ በተለይም አርሶ አደሮችን በያዙ ከሰሃራ በታች ባሉ ሃገራት የምግብ ምርት ብክነት የሚከሰተው ከእርሻ እስከ ገበያ ድረስ ባሉት ሂደቶች መሆኑን ያተተው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰነድ አመታዊ ብክነቱ እስከ 4 ቢሊየን ዶላር የሚደርስና 48 ሚሊየን አፍሪካውያንን አመቱን ሙሉ በበቂ ሁኔታ የሚመግብ ከመሆኑም በላይ በአህጉሪቱ ሊከሰት የሚችለውን አስፈላጊ ያልሆነ የዋጋ መናር ትርጉም ባለው መልኩ ሊቀንስ ይችል ነበር ብሏል። 

በአለም አቀፉ የርሃብ ማሳያ ምደባ መሰረት ከ116 የአለም ሃገራት ውስጥ 90ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ኢትዮጵያ ሁሉም አይነት ከምግብ ጋር የተያያዙ ችግሮችን እያስተናገደች ሲሆን ከፈረንጆቹ 2000 ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ለምግብ የሚያወጡት ወጪ ከገቢያቸው አንጻር ሲታይ አለቅጥ እያሻቀበ ከመሆኑም በተቃራኒ ገበያው ላይ የሚያገኙት ምግብም በመጠን፣ በጥራት፣ በያዛቸው ጠቃሚ ንጥረነገሮች እያሽቆለቆለ መሆኑን ይፋ አድርጓል።   

በሰሜንና በምእራብ ኢትዮጵያ ካለው ጦርነት በተጨማሪ የበረሃ አንበጣ መስፋፋት፣የአየር ጸባይ መለወጥ፣ ጎርፍና ድርቅ እንዲሁም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የመንግስትን ወጪ በከፍተኛ ደረጃ ከመንካታቸውም በላይ የገቢና የወጪ ንግድ ሚዛኑን ላይ ከባድ ተጽእኖ በመፍጠር አዛብተውታል የተባለ ሲሆን የሩሲያና የዩክሬይን ጦርነትም የምግብ አቅርቦት ላይ ሌላ ራስምታት በመጨመር እንደሌሎቹ ሃገራት ሁሉ በኢትዮጵያ መንግስት ላይም ስራ እያበዛበት ነው ተብሏል።  

ሁኔታዎች በዚሁ ከቀጠሉ ከኢትዮጵያ ጥቅል አመታዊ ምርት ውስጥ 16 ነጥብ5 በመቶ የሚሆነው ለምግብ ነክ ድጎማዎች ወጪ ሊደረግ እንደሚችልና የህጻናት የምግብ እጥረትና መቀንጨርን ለመከላከል በሚል መንግስት የሚያወጣውን ወጪ ወደ 55 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር እንደሚያደርሰው የተገለጸ ሲሆን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ 2 ሚሊየን የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ጨምሮ ቀጥተኛ የመንግስት ድጋፍ ፈላጊዎች ቁጥር 12 ነጥብ 8 መድረሱ የአደባባይ ሚስጥር ነው።

ከዩክሬኑ ጦርነት በፊት ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መዛመትና በአንዳንድ አህጉሪቱ አገራት የተፈጠሩ ግጭቶች ከመስፋፋታቸው ጋር በተያያዘ የአፍሪካ የምግብ ምርት ክምችትና አቅርቦት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር ያስታወሱት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት አፍሪካ በምግብ አቅርቦት ራሷን እንድትችል መልካም አጋጣሚ ማምጣቱን መግለጻቸው ይታወሳል።

በአፍሪካ ያለው ሰፊ የእርሻ መሬትና የውሃ ሃብት የተጀመረው ዲጂታል ኢኮኖሚ በራሱ መንገድ ላይ እየተጓዘ በመሆኑ ወጣቶችን ከግብርና ስርአት ጋር ይበልጥ በማቀራረብ የምግብ እጥረትን ማስወገድና ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር እንደሚቻል በማስገንዘብ ችግሮችን ወደ መልካም አጋጣሚ ለመቀየር መትጋት እንደሚያስፈልግ አቶ ኃይለማርያም አስምረውበታል።

ኢትዮጵያ ከጥቂት አመታት በፊት ያስጀመረችው የበጋና የቆላ ስንዴ እርሻ እንዲሁም የከተማ ግብርና ስራዎች ከውጭ ሃገራት የሚመጣውን የምግብ ምርትና ለግዢ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ከማስቀረቱም ጎን ለጎን በሃገር ውስጥ ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ወደ ውጪ የሚደረገውን ስደት ለመቀነስ ብሎም ገበያውን በማረጋጋት የሃገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማስቀጠልና የምግብ ሉአላዊነትን ለማስጠበቅ የሚኖረው አስተዋጽኦ ጉልህ ነው በሚል መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራበት ይገኛል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም