በኃይማኖት ሽፋን ግጭት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አካላት የትኛውንም ኃይማኖት አይወክሉም- የኃይማኖት አባቶች

81

መቱ ሚያዝያ 22/2014 (ኢዜአ)_ ኅብረተሰቡን በኃይማኖት ሽፋን በማጋጨት ለመለያየት የሚንቀሳቀሱ አካላት የትኛውንም ኃይማኖት የማይወክሉ በመሆናቸው አጥብቀው እንደሚያወግዟቸው የኢሉባቦር ዞን የኃይማኖት አባቶች አስታወቁ።

በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ የሚመክር ከዞኑ ሁሉም ወረዳዎች የተወጣጡ የተለያዩ የኃይማኖት አባቶች የተሳተፉበት መድረክ በመቱ ከተማ ተካሄዷል።

የኃይማኖት አባቶቹ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት መንግሥት በኃይማኖት ሽፋን ኅብረተሰቡን ለመለያየት እኩይ ተግባር በሚፈፅሙ አካላት ላይ አስተማሪ የሆነ ህጋዊ እርምጃ ሊወስድ ይገባል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ብዝኃነትን አቻችላ ለዘመናት የኖረችውን ሀገራችንን ለማፍረስ ያደረጉት ሙከራ  አልሳካ ሲላቸው ኃይማኖትን ሽፋን አድርገው የሚንቀሳቀሱትን ነቅተን መመከት አለብን ብለዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የኢሉባቦር ሀገረ ስብከት ምክትል ስራ አስኪያጅ ቀሲስ ታከለ ዳዲ እንዳሉት "በክርስቲያኖችና በሙስሊሞች መካከል ያለው ልዩነት የተለያየ ኃይማኖት መከታላችን እንጂ በሌላ በብዙ ነገር የተጋመድን ነን" ሲሉም ነው በአጽኖት የገለጹት።

አንድ ከሚያደርጉን ከበርካታ ጉዳዮች ይልቅ ጥቂት ነገሮችን በማራገብ በወንድማማቾች መካከል ጠላትነትን የሚሰብኩትን አንድ ሆነን ማውገዝ ይገባናል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ሙስሊም ወንድሞቻችን ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም ጥቃት አጥብቀን እንቃወማለን፤ እናወግዛለንም ብለዋል ቄስ ታከለ።

የሁሉም ኃይማኖት መርህ ሰላምን መስበክ በመሆኑ ጥቃት የሚያደርሱ አካላትና ተግባራቸው የትኛውንም ኃይማኖት የማይወክል መሆኑን ገልፀዋል።

መንግሥትም በኃይማኖት ሽፋን የሚፈጠሩ ችግሮች ሁሉንም የሚነኩ በመሆናቸው ፈጥኖ መፍትሄ ማበጀት አለበት ብለዋል።

የመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ቄስ ደሳለኝ ደገፉ እንዳሉት ሰሞኑን በኃይማኖት ሽፋን የደረሰው ጉዳት የትኛውንም ኃይማኖት አይወክልም።

ተግባሩ በሁሉም ሰው ሊወገዝ የሚገባው ሴራ ነው ያሉት ቄስ ደሳለኝ የክርስትናም ሆነ የእስልምና ኃይማኖት አባቶች ችግሩን በምዕመኖቻችን ውስጥ ለማስፋፋት እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በጋራ ማክሸፍ አለብን ብለዋል።

የቆየ አብሮነታችንንና አንድነታችንን ለማደብዘዝና ዓላማቸውን ለማሳካት  ከሚሰሩ አካላት ምዕመኖቻችን ራሳቸውን እንዲጠብቁና እርስ በርሳቸውም እንዲጠባበቁ የመስራት ኃላፊነታችንንም መወጣት ግድ ይለናል ብለዋል።

የመቱ ከተማ መጅሊስ ኃላፊ ሼህ ኤልያስ መሐመድ በበኩላቸው በተለያዩ ጊዜያት በኃይማኖት ስም በዜጎችና በቤተ እምነቶች ላይ የሚፈፀምን ጥቃትና ጉዳት በጊዜው በመለየትና አፋጣኝ የሕግ እርምጃ በመውሰድ ረገድ በመንግሥት በኩል ክፍተት አለ ይላሉ።

በተለያዩ ጊዜያት ተመሳሳይ ድርጊት ፈፅመውና በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሰው የሚያዙት ጉዳያቸው ተጣርቶ አስተማሪ እርምጃ ተወስዶባቸው ኅብረተሰቡ እንዲያውቅና እንዲማርበት ሲደረግ አይስተዋልም ብለዋል።

በወንድማማችነት የኖረውን ሕዝብ ለመለያየት የሚደረገውን ጥፋት ማርገብ ኃላፊነቱ የኃይማኖት አባቶች ብቻ አድርጎና ጠቅልሎ ማየትም አያስፈልግም ብለዋል።

ችግር የሚፈጥሩ አካላት በየትኛውም ኃይማኖት ጥላ ስር እንዲሁም በመንግሥት መዋቅርም ውስጥ መኖራቸው እሙን ነው ያሉት ደግሞ ሼህ ታጁዲን አብደላ ናቸው።

በመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ ሆነው ሕዝቡን በኃይማኖት የመለያየት ስራ በስውርና በግልፅ የሚሰሩ አካላት ላይ መንግሥት አጣርቶ እርምጃ በመወሰድ ለሕዝቡ ማሳወቅ አለበትም ብለዋል።

ጥላቻን እየሰበኩ በሕዝቡ መካከል መለያየትንና ጥፋትን የሚያስከትሉትን ምዕመኑም ጠንቅቆ መለየት አለበት ሲሉም ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።

የሁሉም ኃይማኖቶች በአንድነት ሆነው በኃይማኖት ሽፋን በዜጎችና በቤተ እምነቶች ላይ የሚፈፀምን ጥፋት እንደሚያወግዙ ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ አንድነት ሰላም ተጠብቆ በኃይማኖት ሽፋን ሕዝብ ለማጋጨት የሚንቀሳቀሱ የአጥፊዎችን ተልዕኮ በጋራ እንዲያከሽፍና ለህግ እንዲቀርቡ የሚጠበቅበትን ሁሉ እንዲያደርግ አሳስዋል።

የኢሉባቦር ዞን አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ በበኩላቸው ሀገርን የማፈራረስ ዓላማቸውን በተለያዩ መንገዶች ሞክረው ያልተሳካላቸውን በኃይማኖት በኩል ሕዝቡን ለመለያየት የሚንቀሳቀሱት ዓላማቸውም በዜጎቻችንብስለትና አንድነት ይከሽፋል ብለዋል።

ይህችን ሀገር ለማፈራረስ የሚሞክሩ አካላት የማይጠቀሙት አማራጭ እንደሌለ ገልጸው ዓላማቸውን ለማክሸፍ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ዜጎች ከስሜታዊነት የነፃ አንድነትና መደማመጥ ወሳኝ መሆኑንም አመልክተዋል።

በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሕዝብን በሕዝብ ላይ ለማነሳሳት የሚነዙትን አንዱን ከሌላው የማጣላት ሙከራዎች ለማን እንደሚጠቅሙ ማጤን ያስፈልጋል ሲሉም አስገንዝበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም