የፌዴራል ፖሊስ ወንጀለኛን የመቆጣጠርና የመከላከል አቅሙ ማደጉን የሚያረጋግጥ ቴክኖሎጂ በፊቼ ጨምበላላ በዓል ተጠቅሟል

254

ሚያዝያ 21 ቀን 2014 (ኢዜአ)የፌዴራል ፖሊስ ወንጀለኛን የመቆጣጠርና የመከላከል አቅሙ ማደጉን የሚያረጋግጥ ቴክኖሎጂ በፊቼ ጨምበላላ በዓል ተጠቅሟል።

በአዲስ አበባ የጎዳና ላይ ኢፍጣር ፕሮግራም በሰላም እንዲካሄድም እየተከታተለ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት ጋር በመሆን በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች የሚደረጉ ሁነቶችን የሚከታተልበት ስርዓት መዘርጋቱ ይታወቃል።

ኮሚሽኑ በመደበኛ ስፍራ የተተከሉና በሰዎች አማካኝነት የሚንቀሳቀሱ ሚስጥራዊ ዘመናዊ ካሜራዎችን ነው እየተጠቀመ የሚገኘው።

ካሜራዎቹ በማዕከል ላይ ከተተከለ መቆጣጣሪያ ክፍል ጋር በቀጥታ የተሳሰሩ በመሆኑ የኮሚሽኑ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ሁነቶቹን በቀጥታ እንዲከታተሉ እድል ፈጥረዋል።

እነዚህ ሚስጥራዊ ካሜራዎች ወንጀልና ወንጀሎኞችን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ መሆናቸውን ነው ኮሚሽኑ የገለጸው።

በኮሚሽኑ የቴክኖሎጂ ማስፋፋያ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ደምሴ ይልማ ለኢዜአ እንደገለጹት የቴክኖሎጂ ውጤቱ ትልቅ ጥቅም እያስገኘ ነው።

ካሜራዎቹ ትናንትናና ዛሬ በደማቅ ሁኔታ በተከበረው የፊቼ ጨምበላላ በዓል ላይ በስፋት ጥቅም ላይ ውለዋል።

በተመሳሳይ በዛሬው የአዲስ አበባ የጎዳና ላይ ኢፍጣር መርሓ ግብርም እነዚሁ ዘመናዊ ሚስጥራዊ ካሜራዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ሰላማዊው ሕዝብ ያለምንም ስጋት እንዲንቀሳቀስ የሚያስችል ነውም ብለዋል።

ኮማንደር ደምሴ አክለውም ሚስጥራዊ ካሜራዎቹ ለነዚህ ሁነቶች ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ወንጀልን መከላከል የሚያስችሉ ናቸው።

ካሜራዎቹ በዚህ ወቅት ዓለም ላይ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ መሆናቸውን ጠቅሰው በማዕከል ያለው የፖሊስ አባልና ቦታው ላይ ያለው ፖሊስ በቀላሉ መረጃ መለዋወጥ እንዲችሉ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።

ይህም መሆኑ ችግሮች ሳይፈጠሩ የመቆጣጠር አቅምን አሳድገዋል ነው ያሉት።እነዚህ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ ካሜራዎች መደረግ ያለበትን ጥንቃቄ ለማደረግ የሚያግዙ ናቸው ብለዋል ኮማንደር ደምሴ።

ይህ ብቻ ሳይሆን ፈጣን እርምጃ ለመውሰድ፣ መንጀለኛን ለፍትህ ለማቅረብም ትልቅ ጥቅም እየሰጡ ነው ብለዋል።

እንደ ኮማንደር ደምሴ ገለጻ የካሜራዎቹ ሚስጥራዊነት በተጠበቀ መልኩና ዘመኑን በሚመጥኑ ቴክኖሎጂዎች ደህንነታቸው ይጠበቃል።

ለዚህም ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሆነ ነው የተናገሩት።

ፖሊስ እየተጠቀመ በሚገኘው ዘመናዊ የደህንነት ቴክኖሎጂዎች አማካኝነት ሰሞኑን በጎንደር በተፈጠረው ችግር ጋር ግንኙነት ያላቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እያዋለ መሆኑም ታውቋል።

በዚህም ከ370 በላይ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም