የኃይማኖት አባቶችን የሰላም ጥሪ በማድመጥና በሰከነ መንገድ በመወያየት በኃይማኖት ሽፋን ለሚፈጠሩ ግጭቶች ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት ይገባል

ሚያዚያ 21/2014/ኢዜአ / የኃይማኖት አባቶችን የሰላም ጥሪ በማድመጥና በሰከነ መንገድ በመወያየት በኃይማኖት ሽፋን ለሚፈጠሩ ግጭቶች ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታወቀ።

ጉባኤው ኃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚከሰቱ ግጭቶችን ጥናትን መሰረት በማድረግ ለመፍታት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሃፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ኃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ ግጭቶች እየተስተዋሉ ነው።  

አማኞች በዚህ እኩይ ሴራ ተጠልፈው ወዳልሆነ ነገር ከመግባት ይልቅ ቆም ብለው ማሰብና ነገሮችን በስክነት መመልከት እንዳለባቸውም  ጥሪ አቅርበዋል።    

"አንድ ሰው ጉዞ ሲጀምር መነሻውና መድረሻውን በአግባቡ አውቆ መሆን አለበት" ያሉት ጠቅላይ ጸሃፊው፤  ወደ ሠላም መንገድ የሚመሩና የሚያስተምሩ አባቶችን በማድመጥ ችግሮችን በሰከነ መንገድ መፍታት ይገባል ነው ያሉት፡፡  

ሃይማኖቶች የአብሮነትና የፍቅር መሰረቶች ናቸው እንጂ የግጭት መንስኤዎች ሊሆኑ አይችሉም ሲሉም  ተናግረዋል፡፡    

ሃይማኖት ጠል የሆኑ ጽንፈኛ ግለሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ሃይማኖት ጠል የሆነ ተቋም ግን የለም ብለዋል፡፡       

"የሃይማኖት ሰዎች ፖለቲካ ውስጥ እንደማይገቡ ሁሉ የፖለቲካ ሰዎችም ሃይማኖት ውስጥ መግባት የለባቸውም፤ ድንበር ሊኖር ይገባል"  ነው ያሉት፡፡        

የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት በተደጋጋሚ ግጭቶች የሚነሱበትን ምክንያት ከመሰረቱ ለመለየት የሚያስችል ጥናት ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።  

እንደ ቀሲስ ታጋይ ገለጻ፤ ጉባኤው ችግሮች ሲከሰቱ ጊዜያዊ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ በዘላቂነት ለመፍታት ወጣቶችን፣ሴቶችንና ጥያቄ ያላቸውን ሰዎች በማነጋገር መፍትሄ እንዲመጣ ይሰራል።

በጥናቱ የሚገኙ ችግሮች ከተለዩ በኋላ ሃይማኖታዊ መፍትሄ የሚያስፈልጋቸው በተቋማት፤ ፖለቲካዊ መፍትሄ የሚያስፈልጋቸው ደግሞ በሚመለከተው አካል የሚታይበት አቅጣጫ ይቀመጣል ነው ያሉት።  

የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሃፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ በበኩላቸው ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሚከሰቱ ግጭቶች የሞራልና ሥነ ምግባር ጉድለቶች አንዱ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።

የሃይማኖት ተቋማት እንደዚህ ዓይነት መሰረታዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ማስተማር፣ መገሰጽና መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል።         

የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ግጭቶች ከመከሰታቸው ቀደም ብለው የመከላከል ስራ ላይ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸውም እንዲሁ።                

ሰላም በአንድ አካል ብቻ የሚመጣ ባለመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበትም አክለዋል።

"ግጭትና ልዩነትን ማቀንቀን ለማንም አይጠቅምም" ያሉት መጋቢ ታምራት፤ ኢትዮጵያን በጋራ ወደፊት ለማስኬድ አንድነትን ማጽናት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል።   

የኢትዮጵያ ዑለማ ምክር ቤት አባል፣ የሰላምና እርቅ ዘርፍ ኃላፊ ሼህ መሃመድ ሲራጅ በኢትዮጵያ ሁሉም ሃይማኖቶች ደስታና ሀዘንን አብረው በጋራ እንደሚያሳልፉ አስታውሰዋል፡፡   

ልዩነት ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት በየትኛውም ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ትልቅ በደል መሆኑን የተናገሩት ሼህ መሃመድ፤ አማኞች እኩይ ዓላማ ለያዙ አካላት በር መክፈት የለባቸውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም