የስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ተሞክሮዎችን በመውሰድ ቀጣዩን ምርጫ የተሳካ ለማድረግ ይሰራል

76

ሚያዚያ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስድስተኛውን አጠቃላይ ምርጫ ሂደት በመገምገም ለቀጣይ ምርጫ ተሞክሮ ለመውሰድ እየሰራ መሆኑን የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አጠቃላይ የምርጫ ሂደትን የሚገመግም የሁለት ቀናት አውድ-ጥናት ዛሬ አስጀምሯል።

የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በወቅቱ እንደገለጹት፤ አውደ-ጥናቱ ስድስተኛውን አጠቃላይ ምርጫ በመገምገም ጠንካራና ደካማ ጎኖችን ለመየት የተዘጋጀ ነው።

ይህንንም ተከትሎ በምርጫው ሂደት የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠልና ክፍተቶችን በመለየት ለሚቀጥለው ምርጫ እንዳይደገሙ ተሞክሮ ለመውሰድ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህም ተሞክሮ በመውሰድ ቀጣዩን ምርጫ የተሳካ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።

አውደ-ጥናቱ በምርጫ የተገኙ ትምህርቶች፣ የግምገማ የጥናት ውጤት የሚተዋወቅበትና የማጠናቀቂያ ግብዓት የሚወሰድበት መሆኑንም ተናግረዋል።

በአውደ-ጥናቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ የመገናኛ ብዙኃንና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ እንደሆኑ ጠቁመዋል።  

በዚህም የስድስተኛው ምርጫ አጠቃላይ ግምገማ በባለድርሻ አካላት ተሳትፎ በተገቢው መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ነው የገለጹት።

የመማማርና የግምገማ ሂደት ቅኝት፣ ተቋማዊ የሪፎርም ሥራና የምርጫ እቅድ፣ የምርጫ አካሄድ የሚሉና ሌሎች ርዕሰ-ጉዳዮች የአውደ-ጥናቱ አጀንዳዎች እንደሆኑ ተገልጿል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም