የድሬዳዋ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በጎንደር ከተማ የተፈጸመውን ድርጊት በፅኑ አወገዘ

82

ድሬዳዋ ሚያዝያ 20/2014 (ኢዜአ).. በኃይማኖት ሽፋን በሀገሪቱ የተፈጠረውን ህብረ-ብሔራዊ እንድነት፣ ሰላምና ህብረት ለማደናቀፍ የሚሞክሩ አካላትን በፅናት እንደሚታገሉ የድሬዳዋ አስተዳደር የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች አስታወቁ።

የድሬዳዋ አስተዳደር የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በጎንደር ከተማ የተፈጸመውን ድርጊት  አውግዘዋል።

የተቋሙ ሰብሳቢ ሊቀብርሃናት ቀለመወርቅ ቢምረው ዜጎችን በእምነት በመከፋፈል ደብቅ የፖለቲካ ፋላጎትን ለማሳካት የሚደረገውን የሽብር ተግባር እንደሚያወግዙ ገልጸዋል፡፡

የእስልምና እና የክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች ሃዘንና ደስታን በጋራ የሚያሳልፉና መስጂዶችንና አቢያተ-ክርስቲያናትን በጋራ በመገንባት ጠንካራ የጋራ ማንነት በመገንባት ዘመን የተሻገሩ ናቸው ብለዋል፡፡

ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ያነገቡ ጥቂት የጥፋት ቡድኖች በጎንደር የፈፀሙትን እኩይ ተግባር በፅኑ እንደሚያወግዙ ገልጸዋል።

ሁለቱንም ሃይማኖቶችና ተከታዮቻቸውን በማይወክሉ ጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች በተፈጸመው አስነዋሪ ድርጊት  ለተጎዱ ወገኖች መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

በቀጣይ የኃይማኖት ተቋማት በጋራ የማነፅና አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረጉ ሥራ የሚጠናከር መሆኑንም አመልክተዋል።

ከዚህም ባሻገር መሰል ጉዳቶች በዜጎችና በንብረት ላይ ዳግም እንዳይደርስ በቅንጅት እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡

የጉባኤው አባል ሼህ ኢብራሂም ኢማም በበኩላቸው በጎንደር በተፈጸመው አስነዋሪ  ድርጊት በድሬዳዋ የእስልምና ከፍተኛ ምክር ቤትና በተቋሙ ስም ሀዛናቸውን ገልጸዋል።

በተፈጸመው ድርጊት  ለተጎዱ ኢትዪጵያውያን  ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡

ከኢትዮጵያውያን ሃይማኖታዊ እሴቶች ውጭ የተፈፀመውን እኩይ ተግባር በፅናት እንደሚያወግዙም ተናግረዋል።

ኃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ድብቅ አጀንዳቸውን ለማሳካት ይህን አስነዋሪ ድርጊት የፈፀሙ ግለሰቦችን መንግሥት ለህግ እንዲያቀርብም  አሳስበዋል፡፡

"ነብስን ያለምንም ምክንያት ማጥፋት በምድርም ሆነ በሰማይ አለም ሃራምና የሚያስጠይቅ የሚያስቀጣ ተግባር ነው" ብለዋል፡፡

ድርጊቱን የፈፀሙ አካላትን ለህግ እንዲቀርቡ ከመጠየቅ ጎን ለጎን  በድሬዳዋ ዘመን የተሻገረውን የሁለቱ ኃይማኖት ተከታዮች የፀና ህብረትና አንድነት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል  እንደሚሰራም  ሼህ ኢብራሂም አረጋግጠዋል፡፡

የጉባኤው ዋና ፀሐፊ ወንድም ሚልኪያስ ታዬ እንዳሉት "ድብቅ ዓላማ ያላቸው አካላት አንድ ጊዜ በብሔር፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በፖለቲካ በህዝቦች መካከል ነውጥ በመፍጠር ስልጣንን  በኃይል ለመያዝ የሚጥሩ ቡድኖች የፈጸሙት ሴራ ነው፡፡"  

እንደ ዋና ፀሐፊው ገለጻ ሀገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍና በህዝቦች መካከል ብጥብጥ ለመፍጠር የሚደረጉ ሀገር አፍራሽ ተግባራትን ጉባኤው በፅናት ይቃወማሉ ብለዋል፡፡

"ምክንያት እየተፈለገ የሀገርን የሰላምና የልማት ጎዳና ማደናቀፍ፣ በዜጎች መካከል ቦታ ሊሰጠው አይገባም" ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

በኃይማኖት ሽፋን በሀገር ሰላምና በህዝቦች ትስስር ላይ ያልተገባ ተጽዕኖ ለመፍጠር በሚሞክሩ አካላት ላይ መንግሥት አፋጣኝ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል።

የጉባኤው አመራሮች በድሬዳዋ የሚገኘውን ህብረ-ብሔራዊ አንድነት፣ ፍቅርና ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም