"ኢትዮጵያ ታምርት" በሚል መሪ ሀሳብ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ችግሮች ለመፍታት ያለመ ንቅናቄ ይካሄዳል

157

ሚያዝያ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ "ኢትዮጵያ ታምርት" በሚል መሪ ሀሳብ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ችግሮች ለመፍታት ያለመ የንቅናቄ መድረክ በመጪው ቅዳሜ እንደሚካሄድ ተገለጸ።

ንቅናቄውን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዣንጥራር አባይ በሰጡት መግለጫ በከተማዋ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚታዮ ችግሮችን የመለየትና መረጃዎችን የማደራጀት ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።

ይህንንም ወደ ተግባር ለመቀየርና ችግሮችን ለመፍታት ያለመ የንቅናቄ መድረክ በመጪው ቅዳሜ ይካሄዳል ብለዋል።

ንቅናቄው በዋነኝነት ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ያሉ በገቢ፣ በተተኪና ወደ ውጭ በሚላኩ ምርቶች ላይ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን ችግር ለመፍታት ያለመ ነው ሲሉ ነው ያብራሩት።

እንደ ሀገር ካሉት አምራች ኢንዱስትሪዎች 40 በመቶዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚገኙ ያመለከቱት ምክትል ከንቲባው ሆኖም ግን በግማሽ አቅማቸው ብቻ እያመረቱ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የሚካሄደው ንቅናቄም በእነዚህ ኢንዱስትሪዎች ላይ የሚታየውን የሀይል አቅርቦት፣ የመሬት፣ የሥልጠና፣ የብድር አቅርቦትና ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት ነው ሲሉ አስታውቀዋል።

አክለውም ንቅናቄው የአምራች ኢንዱስትሪውን አቅም ለመገንባትና የሀገር ውስጥ ተተኪ ምርቶችን ለማሳደግ አወንታዊ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

የፊታችን ቅዳሜ ሚያዝያ 22 ቀን 2014 በሚካሄደው ንቅናቄ የኢንዱሰትሪዎች ጉብኝትና የዘርፉን ችግሮች እንዲሁም መፍትሔ የተመለከተ ውይይት ይካሄዳል ተብሏል።

በንቅናቄው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፣ ባንኮችና የዘርፉ ተዋናዮች እንደሚሳተፉ ተመልክቷል።

በአዲስ አበባ ከተማ ከ10 ሺህ በላይ አነስተኛ መካከለኛና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንደሚገኙ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም