የአክሱም ጽዮን ማሪያም ቤተክርስቲያን ለተፈናቃይ ወገኖች የ200 ሺህ ብር ድጋፍ አደረገች

134
አክሱም ጶግሜ 2/2010 የአክሱም ጽዮን ማሪያም ቤተክርስቲያን ከተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የሚውል ከ200 ሺህ ብር በላይ ለገሰች፡፡ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብም ለተፈናቀሉ ወገኖች መርጃ የደሞዛቸውን 10 በመቶ ለመስጠት ቃል ገብተዋል። የቤተክርስቲያኗ ሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቀመንበር ቦክረ ሊቃውንት ጎደፋ መርሃ እንዳሉት ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አክሱም የሚገኙ ወገኖችን ለመርዳት በሚደረግ ጥረት ቤተክርስቲያኗ  የድርሻዋን ትወጣለች፡፡ ከምእመኑ የተሰበሰበ 200 ሺህ ብር ለዚሁ አገልግሎት እንዲውል ለአክሱም ከተማ ሰራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ማስረከቧን ገልጸዋል። ''በወገኖቻችን  ላይ የደረሰው  ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር  ለመቅረፍ ሁሉም ህብረተሰብ  እጁን ሊዘረጋ ይገባል'' ብለዋል፡፡ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታየውን አለመረጋጋት  ለማስቆምም  ሁሉም ዜጋ ለሰላም ዘብ እንዲቆምና ስለ ሰላም እንዲጸልይ አሳስበዋል፡፡ የአክሱም ከተማ ሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሃንስ ገብረእግዛብሄር በበኩላቸው ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የተፈናቀሉ ከ2ሺህ በላይ ወገኖች አክሱም ከተማ አንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ቤተክርስቲያኗ  ያደረገችው የ200 ሺህ ብር ድጋፍ  በቀጣይ ሳምንት በከፍተኛ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች እንደሚከፋፈልም ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ተፈናቃዮችን ለመደገፍ ኮሚቴ አቋቁሞ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገልጿል። የኮሚቴው አስተባባሪ መምህር ሲሳይ ተክለሃይማኖት እንደተናገሩት የዩኒቨርሲቲው ፈቃደኛ ሰራተኞች የደሞዛቸው 10 በመቶ ለተፈናቃዮች እንዲሰጥ ወስነዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም