'ከኢድ እስከ ኢድ ወደ ሃገር ቤት ጉዞ' ጥሪ መሰረት ወደ አገር ለገቡ ኢትዮጵያውያን 'እንኳን ደህና መጣችሁ' መርሃ ግብር ተካሄደ

109

ሚያዚያ 19/2014 (ኢዜአ) 'ከኢድ እስከ ኢድ ወደ ሃገር ቤት ጉዞ' ጥሪ መሰረት ወደ አገር ለገቡ ኢትዮጵያውያን የ'እንኳን ደህና መጣችሁ' መርሃ ግብር በወዳጅነት አደባባይ ተካሄደ።

በመርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የወጪ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዘዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እንድሪስ እና ከተለያዩ የዓለም አገራት የመጡ ዲያስፖራዎችም ታድመዋል።

በመረሃ ግብሩ ላይ አቶ ደመቀ ለዲያስፖራዎች፣ ለትውልደ ኢትዮጵያውያንና ለኢትዮጵያ ወዳጆች የ'እንኳን ደህና መጣችሁ' መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዚህም ጥሪው የኢትዮጵያን ገፅታ ለመገንባትና የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ወደ አገር ቤት ጥሪው ለዲፕሎማሲ ስራውም ትልቅ አቅም እንደሚሆን ነው የተናገሩት።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አበቤ በበኩላቸው "ዲያስፖራው በአሁኑ ወቅት የሚያኮራ ተግባር እየፈፀመ ይገኛል" ብለዋል።

ይህ መድረክም ወገንን ያኮራው የዲያፖራው ተግባር ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እንድሪስም እንዲሁ በአገር ጉዳይ ላይ እየተመካከሩ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ተቀዳሚ ሙፍቲው የመመካከርና የመተባበር ትርፉ ሰላምን ማረጋገጥ ነው ብለዋል።

በመሆኑም እንደ ሃገር አልፎ አልፎ የሚታዩ ግጭቶችን ለማስቆም ሁሉም መጣር ይኖርበታል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም