በሃይማኖት ሽፋን ሊያጋጩን የሚሹ ቡድኖችን አንድ ሆነን እንታገላቸዋለን- በጎንደር የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታዮች

187

ጎንደር ፤ ሚያዚያ 19/2014 (ኢዜአ) በሃይማኖት ሽፋን ሊያጋጩንና ሊያለያዩን የሚሹ ቡድኖችን አንድ ሆነን አጥብቀን እንታገላቸዋለን ሲሉ በጎንደር ከተማ የሚኖሩ የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታዮች አሰታወቁ፡፡

በከተማው የተፈጠረውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ  የሃይማኖት አባቶችና የእምነቶቹ  ተከታዮች የጋራ ምክክር መድረክ አካሂደዋል፡፡

ከመድረኩ ተሳታፊዎች  መካከል  አቶ መንገሻ ዘውዱ እንዳሉት ሁለቱ የእምነት ተቋማት ገናና ታሪክና ዘመን ተሻጋሪ የአብሮነት እሴት የገነቡ ናቸው፡፡

ሆኖም እኩይ ዓላማ ያላቸው ሃይሎች በሃይማኖት ሽፋን ግጭት  እንዲፈጠር በማድረግ የሁለቱን እምነት ተከታዮች ለመለያየት ያደረጉት ጥረት በማንኛውም መንገድ አይሳካም ሲሉ ገልጸዋል።

ወንድማማችነትና አብሮነትን የገነባ ህብረተሰብ በችግርም ሆነ በደስታ ጊዜ ከቶም አይለያይም ያሉት ደግሞ አቶ እሸት አበበ ናቸው፡፡

የጥፋት ቡድኖች በሃይማኖት ሽፋን ሊከፋፍሉን ቢፈልጉም እኛ በአንድነታችንና አብሮነታችን አንለያይም ብለዋል፡፡

የበለጠ በመተባበርና በመተጋገዝ  የጥፋት ቡድኖች እኩይ ዓላማቸውን ሙሉ በሙሉ ለማክሸፍ እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

የተፈጠረው ግጭት ታሪካዊ ጠላቶቻችን የሸረቡልን ወጥመድ በመሆኑ በጋራ አጥብቀን እንታገላቸዋለን ያሉት ደግሞ አቶ ሱሌማን ዳውድ ናቸው።

በመካከላችን መከፋፈልንና መጠፋፋትን ለማንገስ የተነሱ አካላትን በጋራ ታግለን እናሸንፋቸዋለን ብለዋል።

ተሳታፊዎቹ እንዳሉት፤ ገናና ታሪክና ስም ያላት ጎንደር እኩይ ዓላማ ባላቸው ቡድች የእምነት ግጭት እንዲፈጠር መደረጉ አሳፋሪና አንገት የሚያስደፋ ድርጊት ነው፡፡

”በማንም ይሁን በምንም የተፈጠረው ችግር በእጅጉ ያሳዝናል” ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ጣሂር መሀመድ ናቸው፡፡

ድርጊቱ በህግ አካል ይጣራል ያሉት አቶ ጣሂር፤ የእምነቱ መሪዎችና ተከታዮች ተቀራርበውና ተወያይተው ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊፈቱ ይገባል ብለዋል፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ጌታቸው ጀንበር በበኩላቸው፤ ድርጊቱ  ልብ የሚሰብር አሳዘኝና ለጠላቶቻችን በር የሚከፍት የጥፋት መልእክተኞች እኩይ ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል፡

ሀገር ለማፍረስ የውስጥም ሆነ የውጭ ጠላቶቻችን በጋራ ባሰፈሰፉበት ወቅት በእምነቶች መካከል ግጭት መፈጠሩ አሳዘኝ  መሆኑን ገልጸው፤የሁለቱም እምነቶች መሪዎችና ተከታዮች የሰላምና የአብሮነት የአንድነት ተምሳሌትነታቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት በግጭቱ በሰው ህይወት ላይ በደረሰው ጉዳት ከባድ ሀዘን እንደተሰማው ገልጸው፤  አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ በሚደረገው የምርመራ ስራ ህዝቡ ወንጀለኞችን በማጋለጥ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በምክክር መድረኩ የክልሉና የጎንደር ከተማ ከፍተኛ አመራሮች፣ ከከተማው የተለያዩ ቀበሌዎች የተውጣጡ የእምነቶቹ ተከታዮችና የሃይማኖት አባቶች መሳተፋቸውን ኢዜአ ከጎንደር ዘግቧል፡፡