የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በጎንደር የተፈጸመውን ጥፋት አወገዘ

173

ባህር ዳር ፤ ሚያዚያ 19/2014(ኢዜአ).የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በጎንደር ከተማ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የተፈጠረው ግጭት የማንኛውንም እምነትና ተከታዮችን የማይወክል የአስነዋሪ ድርጊት በመሆኑ አጥብቆ እንደሚያወግዘው አስታወቀ።

የጉባኤው የቦርድ ሰብሳቢ ተወካይ መላከ ብርሃን ፍሰሃ ጥላሁን በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ የተፈጠረው ችግር  ሀገሪቱና ክልሉ ያለበትን ሁኔታ ያላገናዘበ አሳፋሪና በሁሉም  ዜጋ የሚወገዝ አስነዋሪ ድርጊት ነው።

ችግሮች ቢኖሩም በሰከነና በሰለጠነ አግባብ በመነጋገር፣ በመመካከርና በመከባበር መፍታት እንደሚገባ ተናግረዋል።

መንግሥት በዚህ አስነዋሪ ድርጊት የተሳተፉ አካላትን በፍጥነት አጣርቶ ለህግ ማቅረብ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋምት ጉባኤ በተፈጠረው ግጭት የተጎዱና ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን  በሚችለው ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የጉባኤው ምክትል ሰብሳቢ ተወካይ ሃጅ የሱፍ ማሩ በበኩላቸው፤ የተፈፀመው ድርጊት የማንኛውንም እምነትና ተከታዮችን የማይወክልና ከኢትዮጽያዊ እሴት ያፈነገጠ አስነዋሪ ድርጊት በመሆኑ ሊወገዝ ይገባል ብለዋል።