የአፍሪካ የዞን 4.4 የቼስ ሻምፒዮና ላይ ለመሳተፍ እስካሁን አምስት ሀገራት ማረጋገጫ ሰጥተዋል

186

ሚያዝያ 19 /2ዐ14 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ የዞን 4.4 የቼስ የግል የበላይነት ሻምፒዮና ላይ ለመሳተፍ እስካሁን አምስት ሀገራት ማረጋገጫ መስጠታቸውን የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ሻምፒዮናው ከሚያዚያ 23 እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

ውድድሩ ከዓለም አቀፍ ቼስ ፌዴሬሽንና ከአፍሪካ ቼስ ኮንፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የሚዘጋጅ እንደሆነም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ቼስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ ሰይፉ በላይነህ፤ ውድድሩን በተሳካ መልኩ ለማካሄድ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ሻምፒዮና ለመሳተፍ እስካሁን አምስት የአፍሪካ ሀገራት ማረጋገጫ መስጠታቸውንም ገልጸዋል።

ማረጋገጫ የሰጡት ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ፣ ጅቡቲና  ሱዳን መሆናቸው ተገልጿል።

በዚህ ሳምንት ሌሎች ተጨማሪ ሀገራት ተሳታፊነታቸውን ያረጋግጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የጠቆሙት

ይህ ውድድር በኢትዮጵያ መካሄዱ የቼስ ስፖርትን የበለጠ ለማስፋፋት የራሱ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያን ባህልና ቱሪዝም ለማስተዋወቅና ለማሳደግም ጉልህ ሚና እንዳለው አንስተዋል።

በዚህ ውድድር እያንዳንዱ ሀገር አምስት ወንድና አምስት ሴት ስፖርተኞችን የሚያሳትፍ ይሆናል።

ኢትዮጵያ አስተናጋጅ ሀገር እንደመሆኗ ሌሎች ከሚያሳትፉት በእጥፍ ስፖርተኞችን ታሳትፋለች።

እንዲሁም አሥር ኢትዮጵያዊያን ስፖርተኞች በአፍሪካ ቼስ ኮንፌዴሬሽን በቀጥታ የተወከሉ ስፖርተኞች ደግሞ በግል ይወዳደራሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያን የሚወክሉ የቼስ ብሔራዊ ቡድን አትሌቶችም በሁለቱም ጾታ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

ይህ የአፍሪካ የ2022 ዓ.ም የዞን 4.4 የቼስ የግል የበላይነት ሻምፒዮና በአዲስ አበባ ማግኖሊያ ሆቴል የሚደረግ ሲሆን ከውድድሩ ጎን ለጎን የቼስ ዳኞች ዓለም አቀፍ ሥልጠና ይሰጣል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም