የመዲናዋ ከፍተኛ አመራሮች እስከታችኛው መዋቅር ድረስ በመውረድ ሥር የሰደዱ ችግሮችን መፍታት አለባቸው

151

ሚያዝያ 19 /2ዐ14 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች እስከታችኛው መዋቅር ድረስ በመውረድ ሥር የሰደዱ ችግሮችን መፍታት እንዳለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አሳሰቡ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዘጠኝ ወር የሥራ አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ተገምግሟል።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የእቅድ አፈጻጸሙን በተመለከተ ባቀረቡት ሪፖርት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡

በተለይ የድህነት ቅነሳ ተግባራት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱንም ነው ከንቲባዋ ያነሱት፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመዲናዋ ከ340 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩን ለአብነት አንስተው፤ ከዚህም ውስጥ 72 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል 1 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ መድቦ መሰረታዊ ሸቀጦች በህብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት እንዲቀርብ መደረጉንም ነው የገለጹት፡፡

በመዲናዋ የእሑድ ገበያዎችን ማስፋፋትም በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ሥራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የከተማ ግብርናን በማስፋፋት ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ የምግብ ምርቶችን እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ከንቲባዋ፤ ለአብነትም በ140 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ እየተገነባ ያለው የከተማ ግብርና ማምረቻ ማዕከል የመጀመሪያ ዙር ግንባታ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡

 ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ አሁንም የከተማዋ ፈተና መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ በህገ-ወጥ መንገድ የተወረረ 383 ሄክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ ገቢ ተደርጓል ነው ያሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው የሕብረተሰቡን የኑሮ ፈተና በማቃለል ረገድ አመራሩ ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት ብለዋል።

በመሆኑም አመራሩ ይህን በመገንዘብ ቀጣይነት ባለው መልኩ የህብረተሰቡን ችግር ለማቃለል መሥራት አለበት ሲሉም ነው ያሳሰቡት፡፡

እያንዳንዱ አመራር “የዜጎችን ኑሮ በምን ያህል ደረጃ ማሻሻል ችያለሁ?” በማለት እራሱን መጠየቅ እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

አመራሩ ችግሮች ያሉባቸው ቦታ ድረስ በመውረድ የህብረተሰቡን የኑሮ ጫና እና ችግር ለማቃለል እንዲሰራም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስገነዘቡት፡፡

በተለይም ሌቦችን በመለየትና እርምጃ በመውሰድ የአገልግሎት አሰጣጡን ፍትሃዊ ማድረግ እንዳለባቸውም እንዲሁ፡፡

በመዲናዋ የጓሮ አትክልት ልማት እንዲስፋፋ አመራሩ አርአያ ሆኖ መስራት እንዳለበት ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህም በከተማዋ የሚስተዋለውን የምግብ ዋጋ ንረት ማሻሻል ይቻላል ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ ለጓሮ አትክልት ልማት ምቹ መሆኗን በማብራራት፡፡