በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተመለከተ

136

ፍቼ ፤ሚያዝያ 19 2ዐ14(ኢዜአ) በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ የሀይል ጥቃትና ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ተመለከተ።

የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ  በሴቶችና ታዳጊ ህፃናት ላይ የሚደርሱ የሃይል  ጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ  የሚያግዝ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ውይይት ዛሬ  በፍቼ ከተማ አካሄዷል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሰሚራ ፋሪስ በወቅቱ እንዳመለከቱት፤ ከአሁን ቀደም በክልሉ ችግሩን ለማስወገድ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር  አበረታች ስራ ቢከናወንም ውጤቱ ከችግሩ ስፋት አኳያ አሁንም ያለው ክፍተት ሰፊ ነው፡፡

ድርጊቱን ለማስቀረት ተሰሚነት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የፍትህ አካላትና መገናኛ ብዙሀን  የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በተለይ የፀጥታ ችግርና ድህነት ጎልቶ ባለባቸው አካባቢዎች ሴቶችና ህፃናት የጥቃት ሰለባ እንዳይሆኑ ከፍትህ አካል በተጨማሪ ተሰሚነት ያላቸው አካላት የድርጊቱን ነውረኝነት በሚያጎላ መልኩ ሊያስተምሩ ይገባል ብለዋል፡፡

ያለ እድሜ ጋብቻ፣ ጠለፋ፣ አስገድዶ መድፈር የመሳሰሉ ጥቃቶች የደረሰባቸው ወገኖች ፍትህ እንዲያገኙና ስነ-ልቦናቸው እንዲጠገን የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች ሚናቸው የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አልፎ አልፎ ክስ እንዲቋረጥና በባህላዊ መንገድ ችግሩ እንዲፈታ የሚያደርጉት ጥረት ተጎጂዎችን ለባሰ ስነ-ልቦና ችግር የሚዳርግ በመሆኑ ሊታረም እንደሚገባውም ጠቁመዋል፡፡

በኦሮሚያ የሰሜን ሸዋ ዞን ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሀላፊ ወይዘሮ መዝገቤ አበበ በበኩላቸው፤ የሴቶችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ የተከናወኑ ስራዎችና የተገኙ ውጤቶች አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሆኖም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በማስወገድ ረገድ ግን ከችግሩ ስፋት አኳያ የተሰራው ስራ ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃቶችን ለመከላከል ብሎም  ለማስቀረት ተከታታይነት ያለው ሁሉ አቀፍ የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግም የተናገሩት ደግሞ  የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ኘሬዚዳንት አቶ ለታ ቦንሳ ናቸው።

በተለይ ጥቃት ከመፈፀሙ በፊትና በኋላ ስለ ችግሩ ለህብረተሰቡ የማስረዳት ስራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡  

ሀደ ስንቄ በየነች ዋቄ በሰጡት አስተያየት፤ በሴቶች ላይ የሚደርስ ያለእድሜ ጋብቻና ጠለፋ ለማስወገድ ተባብሮና ተደራጅቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ከምስራቅና ምዕራብ፣ ሰሜንና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች የተውጣጡ የፍትህ አካላት ፣ሴቶችና ወጣቶች መሳተፋቸውን ኢዜአ ከፍቼ ዘግቧል፡፡