የምሥራቅ አፍሪካ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት በቀጣናው ግጭትን የመከላከል ዲፕሎማሲ እንዲጠናከር ያስችላል

150

ሚያዝያ 19 / 2014 (ኢዜአ) የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የአገር ሽማግሌዎች መማክርት በቀጣናው ግጭትን ቀድሞ የመከላከል ዲፕሎማሲ ማጠናከር እንደሚያስችል የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ።

የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የአገር ሽማግሌዎች መማክርትን ባሳለፍነው ታህሳስ ወር ላይ ነበር የቀጣናው አገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች ያጸደቁት።

መማክርቱም የሥራ ማስጀመሪያ ጉባኤውን ዛሬ በአዲስ አበባ አካሂዷል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ግጭትን መከላከል ምጣኔ ሃብታዊም ይሁን በሌሎች መስፈርቶች አዋጭ አካሄድ ነው።

የአፍሪካ ኅብረት አስቀድሞ የሽማግሌዎች መማክርት ማቋቋሙን ጠቁመው፤ አሁን ደግሞ የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የራሱን መማክርት ማቋቋሙን ወሳኝ ነው ብለዋል።

ይህም በቀጣናው ግጭትን የመከላከል ዲፕሎማሲ እንዲጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የጀመረው ግጭትን የመከላከል ዲፕሎማሲ በቀጣናው ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና እንዳለውም ነው የጠቆሙት።

ሽማግሌዎች ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል እሴት እንዳላቸው ተናግረው፤ በሚያካሂዷቸው  የእርቅ ሥልቶች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።  

ሽማግሌዎቹ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችል አቅም እንዳላቸው ገልጸው፤ ለስኬታቸውም የኢትዮጵያ መንግሥት ከጎናቸው እንደሚቆም አረጋግጠዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ዋና ጸሐፊ ብርጋዴር ጄነራል ጌታቸው ሽፈራው በበኩላቸው፤ የተቋቋመው የሽማግሌዎች መማክርት ለቀጣናው ሰላም ትልቅ እምርታ አለው።

 በአካባቢው የሚስተዋሉ የአገር ውስጥ የእርስበርስና የአገራት ግጭቶች እንዳይከሰቱ በማድረግ ዘላቂ ሰላምና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።

በተለይም የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ደኅንነት ፍኖተ ካርታ የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የሰላም እንቅስቃሴዎች በጋራ በተናበበ መልኩ ገቢራዊ ለማድረግ ያስችላል ነው ያሉት።

ይህንን እውን ለማድረግ ሽማግሌዎቹ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያረጋገጡት።