ከኢድ እስከ ኢድ መርሃ-ግብር የኢትዮጵያን ምስል በዓለም አደባባይ ማሳየት የሚያስችል ልዩ አጋጣሚ ነው

175

ሚያዝያ 19 / 2014 (ኢዜአ) "ከኢድ እስከ ኢድ የታላቁ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት" መርሃ-ግብር በተለያየ መልኩ የኢትዮጵያን መልካም ስም በዓለም አደባባይ ማሳየት የሚያስችል ልዩ አጋጣሚ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ።

10ኛው ዙር የኢድ-ኤክስፖ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በዛሬው ዕለት በይፋ ተከፍቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ እና ከኢድ እስከ ኢድ አዘጋጅ ብሔራዊ ጥምር ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፤ በመክፈቻ መርሃ-ግብሩ ላይ በመገኘት መልእክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ በተለያዩ አገራት ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ- ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ኢድን በጋራ ለማክበር አገር ቤት እንዲገኙ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

በዚህም መሰረት እንግዶች ወደ አገር ቤት በመግባት ላይ ሲሆኑ ዳያስፖራዎች በዓሉን በጋራ እያከበሩ ለአገራቸውና ለወገናቸው የሚችሉትን አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በመሆኑም "ከኢድ እስከ ኢድ የታላቁ ጉዞ ወደ ሀገር ቤት" መርሃ-ግብር የኢትዮጵያን ምስል በዓለም አደባባይ ማሳየት የሚያስችል ልዩ አጋጣሚ መሆኑን አምባሳደር ብርቱካን ተናግረዋል።

አጋጣሚው ዳያስፖራዎች አገራቸውንና ህዝባቸውን በብዙ መልኩ እንዲያግዙ የሚያስችላቸው መሆኑንም ነው የገለጹት።

በዓሉን በማስመልከት በተዘጋጀው ኤክስፖ ዳያስፖራዎች በመጎብኘትና በመሸመት የኢትዮጵያን ምርት እንዲያስተዋውቁም አምባሳደር ብርቱካን ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እንድሪስ፤ የኢድ-ኤክስፖን በማስመልከት ኤጀንሲው ለዳያስፖራው ጥሪ ማድረጉን ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ወደ አገር ቤት በመግባት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ለአገርና ወገናቸው የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የሃላል ፕሮሞሽን የቦርድ ሰብሳቢ ፈይሰል ከማል፤ ኤክስፖው በዓሉን መሰረት በማድረግ ብዙ የገበያ አማራጮች የቀረቡበትና የአገር ምርት የሚተዋወቅበት መልካም አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።

የዘንድሮው የኢድ-ኤክስፖ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 24 ቀን 2014 ዓ.ም.የሚቆይ ሲሆን ከ200 በላይ ነጋዴዎች ምርታቸውን ይዘው የሚቀርቡ መሆኑ ታውቋል።

በኤክስፖው ከህንድ፣ ሶሪያ፣ ቱርክ እና ሌሎችም አገሮች ምርታቸውን ይዘው የቀረቡ ኩባንያዎች መኖራቸው ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም