በክልሉ የ90 ቀናት እቅድ አፈጻጸም ተከታትሎ ለህዝብ የሚያሳውቅ የሚዲያና ኮመዩኒኬሽን ግብረ ኃይል ተቋቋመ

143

አሶሳ፤ ሚያዝያ 19 / 2014 (ኢዜአ)በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለህብረተሰቡ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የተዘጋጀውን የ90 ቀናት እቅድ አፈጻጸም ተከታተሎ ለህዝብ የሚያሳውቅ የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ግብረ ኃይል ተቋቋመ፡፡

በህዝብ ይሁንታ አግኝቶ መንግስትን እንዲመራ የተመረጠው የብልጽግና ፓርቲ የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ  ሲሆን፣ የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤትና በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የሚዲያ አካላት ደግሞ አባላት ናቸው፡፡

የብልጽግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል  የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊና የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ አቶ ካሚል ሃሚድ እንዳስረዱት፤ ግብረኃይሉ ከህዝብ የተነሱ መሠረታዊ ጥያቄዎችን መመለሳቸውን አስመልክቶ ተገቢው መረጃ እንዲወጣ ይሰራል፡፡

በክልሉ በተካሄዱት ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ከተለዩት ችግሮች መካከል የጸጥታ፣ የኑሮ ውድነትና መልካም አስተዳደር በዋነኝነት ጠቅሰዋል።

በክልሉ  ለጥያቄዎቹ  ምላሽ ለመስጠት  የ90 ቀናት እቅድ መዘጋጀቱን  አቶ ካሚል ገልጸው፤ ግብረ ኃይሉ የዕቅዱን አፈጻጸም በተመለከተ የሚመለከታቸው አመራሮች በመገናኛ ብዙሃን በኩል ለህብረተሰቡ መረጃ እንዲሰጡ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በአፈጻጸማቸው ላይ መረጃ የማይሰጡ አመራሮች ወይም ባለሙያዎች ካሉ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት በማድረግ ተጠያቂ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል፡፡

እንደ አስፈላጊነቱ ወደ ህብረተሰቡን በማነጋገር በእቅዱ አፈጻጸም የተከሰቱ ችግሮች ካጋጠሙ አስቸኳይ የማስተካከያ  እርምጃ እንዲወሰድ ለሚመለከታቸው አካላት መረጃ እንደሚሰጥም አመልክተዋል፡፡

ግብረ ኃይሉ እንደአስፈላጊነቱ በተዋረድ አደረጃጀቶች ሊኖሩት እንደሚችሉ አቶ ካሚል ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊና የግብረ ኃይሉ ምክትል ሰብሳቢ አቶ መለሰ በየነ፤ በክልሉ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን የህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

በሃገራዊም ሆነ ክልላዊ እቅዶችን በመተግበሩ ሂደት  የሚያጋጥሙ ችግሮች እንዲፈቱ መገናኛ ብዙሃን መፍትሄዎች ማመላከት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡

ግብረኃይሉም መገናኛ ብዙሃን ተገቢውን መረጃ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚሰራ አቶ መለሰ አስረድተዋል፡፡

ግብረ ኃይሉ በየወሩ የዕቅዱን አፈጻጸም እንደሚገመግም ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም