የመረዳዳት፣ የመደጋገፍና የአብሮነት እሴቶች ተጠብቀው ለትውልድ መሸጋገር አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የመረዳዳት፣ የመደጋገፍና የአብሮነት እሴቶች ተጠብቀው ለትውልድ መሸጋገር አለባቸው

ሚያዝያ 19/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያዊያን የመረዳዳት፣ የመደጋገፍና የአብሮነት እሴቶች ተጠብቀው ለትውልድ መሸጋገር አለባቸው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች፣ የፌደራልና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የአብሮነት ማእድ ፕሮግራም ተካሂዷል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የኢትዮጵያን መልካም እሴቶች በማጎልበት ትውልድን በመልካም ስነ-ምግባር ማነጽ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህ ደግሞ የሃይማኖት አባቶች ትልቅ አደራ እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ የመረዳዳት፣ የመደጋገፍና የአብሮነት እሴቶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲሻገሩ ሁላችንም መሥራት አለብን ብለዋል።
አብሮነትን በማጠናከር ብዝሃነትን አክብሮ መንቀሳቀስ ከየትኛውም ጊዜ በላይ ለኢትዮጵያዊያን አስፈላጊ መሆኑንም ከንቲባዋ ገልጸዋል።
የሃይማኖት አባቶች ለሰላምና አብሮነት መጎልበት እያደረጉት ላለው አስተዋጽኦ አመስግነው ቀጣይነት እንዲኖረውም ጠይቀዋል።
"በጋራ ማዕድ መቋደሳችን የአብሮነት፣ የአንድነት፣ የመተሳሰብና በአንድ ጥላ ሥር የመኖር እሴት መገለጫ አንዱ ማሳያ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያዊያን የቆዩ እሴቶች መከባበርና መተጋገዝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጥላቻ እና ዋልታ ረገጥ ቅራኔ ጥፋት እንጂ ትርፍ ስለማይኖረው ለአብሮነታችን በጋራ እንቁም ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።