ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ በሰቆጣ የስደተኞች መጠለያ ያነሳሁትን ፎቶ ቦታና ጊዜ በመለወጥ አሳስቶ ለአምንስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዎች የጋራ ሪፖርት ማሳያ አድርጎ ተጠቅሞበታል - ጀማል ካውንተስ

219

ሚያዚያ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) “ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ በሰቆጣ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ያነሳሁትን ፎቶ ቦታና ጊዜ በመለወጥ በማሳሳት ለአምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዎች የጋራ ሪፖርት ማሳያ አድርጎ ተጠቅሞበታል” ሲል አሜሪካዊው ፎቶ አንሺ ጀማል ካውንተስ ገለጸ።

“አንዳንድ ምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃኖች ከዚህ በፊት በአማራና አፋር ክልሎች ያነሳኋቸውን ፎቶዎች በትግራይ ክልል እንደተነሱ አድርገው ሲጠቀሙ ነበር” ብሏል።

የብሪታኒያው ዕለታዊ ጋዜጣ ዘ ጋርዲያን እ.አ.አ ሚያዚያ 6 ቀን 2022 አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዎች በጋራ ያወጡትን ሪፖርት በተመለከተ ዘገባ አውጥቶ ነበር።

ጋዜጣው ለዘገባው የተጠቀመበት ፎቶ እ.አ.አ መጋቢት 30 ቀን 2022 በዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ሰቆጣ ከተማ መብራት ኃይል እየተባለ በሚጠራ የመጠለያ ጣቢያ ያነሳው እንደሆነ በጌቲ ኢሜጅስና በሌሎች ተቋማት በፎቶ አንሺነት የሚሰራው ጀማል ካውንተስ ለኢዜአ ገልጿል።

ወደ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያው ሁለት ጊዜ ያቀናው ጀማል ካውንተስ፤ በመጀመሪያ ጉዞው ፎቶውን እንዳነሳ አመልክቷል።

በመጠለያ ጣቢያው የሚገኙ ተፈናቃዮች ሕወሓት ፈጽሞት በነበረው ወረራ የተፈናቀሉና ወደ ቀዬአቸው መመለስ እንዳልቻሉ እንደገለጹትም ተናግሯል።

ከተፈናቃዮቹ አብዛኞቹ ከስድስት ወር በፊት ሕወሓት በዞኑ በፈጸመው ወረራ ተፈናቅለው ባህርዳር በሚገኘው “ዘንዘልማ” በሚሰኝ መጠልያ ጣቢያ ውስጥ እንደነበሩ አስታውሶ፤ በወቅቱ በቦታው ሄዶ ለማየት መቻሉን አመልክቷል።

ይሁንና ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ “በመጠለያ ጣቢያው ያነሳሁትን ፎቶ ቦታና ግዜውን አጥፍቶ በተሳሳተ መልኩ ለአምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዎች የጋራ ሪፖርት ለማሳያና ለማጉያ አድርጎ ተጠቅሞበታል” ብሏል።

ጋዜጣው ፎቶውን ሲጠቀምም የጌቲ ኢሜጅስ ድርጅትን አርማና ፎቶው የተነሳበትን ጊዜና ቦታ አጭር መግለጫ በማጥፋት ለዘገባው እንደተጠቀመበት በመግለጽ አጋልጧል።

“ጋዜጣው የፈጸመው ድርጊት የስንፍና ጋዜጠኝነት ማሳያና የጋዜጠኝነት ሙያ ስነ ምግባርን የጣሰ ነው፤ ከጀርባው እኩይ የሆነ አጀንዳን የማስፈጸምን ፍላጎትን ይዟል” ሲል ጀማል ካውንተስ ገልጿል።

ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ ውሸትን እውነት አድርጎ ለማሳየት የፈጸመው ድርጊት መወገዝ እንዳለበት ተናግሯል።

ጋዜጣው የፈጸመውን ድርጊት ለጌቲ ኢሜጅስ በማሳወቅ ድርጅቱ ለመገናኛ ብዙሃኑ ጥያቄ እንዲያቀርብ መጠየቁን አመልክቷል።

ኢዜአ ይህን ዘገባ ባጠናቀረበት ወቅት የብሪታኒያው ዕለታዊ ጋዜጣ ዘ ጋርዲያን እ.አ.አ ሚያዚያ 6 ቀን 2022 ለሰራው ዘገባ የተጠቀመበትን ፎቶ በማውረድ በሌላ ፎቶ መተካቱን ለመረዳት ችሏል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል እ.አ.አ በሐምሌ ወር 2021 “አዲስ አበባ አበባ እስር ቤቶች አላግባብ እየታሰሩ ባሉ ትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ተሞልተዋል፤ እስሩም ብሔርን መሰረት ያደረገ ነው” በሚል ያወጣው ሪፖርት የተጠቀመበት ፎቶ የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ፎቶግራፈር አማኑኤል ስለሺ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት በስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ድምጽ ለመስጠት የተሰለፉ ሰዎች ሲፈተሹ ያነሳው ፎቶ ሆኖ መገኘቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም