በመዲናዋ የፊታችን ዓርብ ታላቅ የጎዳና ላይ ኢፍጣር ይካሄዳል

89

ሚያዚያ 18/2014/ኢዜአ/ የፊታችን አርብ ሚያዚያ 21 ቀን 2014 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ በአዲስ አበባ ከተማ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚሳተፉበት ታላቅ የጎዳና ላይ ኢፍጣር እንደሚካሄድ የኢድ እስከ ኢድ ብሔራዊ ጣምራ ኮሚቴ አስታወቀ።

ኮሚቴው ታላቁን የጎዳና ላይ ኢፍጣር እና የኢድ ሰላት በደማቅ ሁኔታ ለማካሄድ በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጿል።

የብሔራዊ ጣምራ ኮሚቴው የኢድ እስከ ኢድ ሀገራዊ ጥሪን ዝግጅትን በሚመለከት ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫውም የኢድ እስከ ኢድ ሀገራዊ ጥሪን ተከትሎ በተለያየ ዓለማት የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገር ቤት እየገቡ ይገኛሉ።

የኢድ እስከ ኢድ ብሔራዊ ጣምራ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዑስታዝ አቡበከር አሕመድ፥ በዓሉን በጋራ በማሳለፍ፣ የተቸገሩ ወገኖችን በማገዝ እና በአብሮነት ለማሳለፍ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የእስልምና እምነትና ኢትዮጵያ ያላቸውን ቁርኝት ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅም የኢድ እስከ ኢድ ሀገራዊ ጥሪ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ገልጸዋል።

በመርሃ-ግብሩ መሰረትም ነገ ረብዑ ከጥዋት ጀምሮ የመጀመሪያው "የኢድ ኤክስፖ" በኤግዚቢሽንና ባዘር  ማዕከል እንደሚካሄድ ጠቁመው፥ ከሰዓት በኋላ ደግሞ ከውጭ ሀገራት በኢድ እስከ ኢድ መርሃ ግብር ለመካፈል ለመጡ እንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም እንደሚኖር ጠቁመዋል፡፡

በሚቀጥለው አርብ ሚያዚያ 21 ቀን 2014 ዓ.ም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በሚገኝበት ታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣር ይካሄዳል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ለመሳተፍ የሚመጣው የአዲስ አበባና ዙሪያዋ ማህበረሰብም ለኢፍጣር የሚሆኑ ምግቦችን ይዞ በመምጣት በዓሉን በአንድነት እንዲያከብር ጥሪ አቅርበዋል።

የኃላል ፕሮሞሽን የቦርድ ሰብሳቢ ፈይሰል ከማል፤ ኢትዮጵያዊ አብሮነትን ለዓለም ማሳየት፣ የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት፣ መተባበር፣ ፈጣሪን በአንድነት መማጸን፣ በጦርነትና ድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት የሚያስችል ገቢ የማሰባሰብ መርኃ ግብር ማካሄድ የዝግጅቱ ዋና ዓላማ መሆኑን አንስተዋል።

በኢድ እስከ ኢድ መርኃ ግብር የመዲናዋን ብሎም የኢትዮጵያን ገጽታ የምናሳይበት ይሆናል ያሉት ደግሞ  የነጃሺ በጎ አድራጎት የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ሰመሃል ተክሌ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጥሪ ተከትሎ በ"ኢድ እስከ ኢድ" መርሃ ግብር ለመሳተፍ የሚመጡ እንግዶችን የሚያስተባብሩ በርካታ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች መዘጋጀታቸውም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም