በአዲሱ ዓመት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለአገሪቱ እድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጥሪ አቀረቡ

120
አዲስ አበባ ጳጉሜ 1/2010 በአዲሱ ዓመት መላው ኢትዮጵያውያን በሚችሉት አቅም ለአገር እድገትና ብልፅግና የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ዛሬ ከአስመራ ሲመለሱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ መግለጫ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው እንዳሉት በኢትዮጵያ የሚፈለገውን ዓይነት ልማትና እድገት ማረጋገጥ የሚቻለው የሁሉም ዜጋ ርብርብ ሲታከልበት ነው። "የምንፈልገውን ልማትና እድገት ለማምጣት አንዱ ተመልካች ሌላው ሰራተኛ መሆን የለበትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሁላችንም በጋራ በመረባረብ የተሻለ ለውጥ ማምጣት ይጠበቅብናል" ብለዋል። በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በአገሩ እድገትና ልማት ላይ የበኩሉን ድርሻ ማበርከት እንደሚገባው ያስገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ የህብረተሰብ ክፍል እስካሁን ሲያደርጋቸው የነበሩትን የልማት እንቅስቃሴዎች አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል። የንግዱ ማህበረሰብን ጨምሮ ሁሉም ባለኃብቶች በአገራቸው ጉዳይ ከበፊቱ የተለየ ኃላፊነትና ሚና እንደሚጠበቅባቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። መላው ባለኃብት ግብር የመክፈል ግዴታው መሆኑን ተገንዝቦ የሚጠበቅበትን ግብር በትክክልና በወቅቱ ለመንግስት ገቢ በማድረግ አገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል። ግብር ሰብሳቢው መስሪያ ቤትም የተሰበሰበው ኃብት በትክክለኛው መንገድ ለልማትና ለአገር እድገት የሚውልበትን መንገድ በማረጋገጥ  ሃላፊነቱን መወጣት እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል። መንግስትም በበኩሉ ወጭ ለመቀነስ፣ የተስተካከለ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋትና የተቋማትን አቅም ለመገንባት  በአዲሱ ዓመት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አስገንዝበዋል። በመጪው ዘመን በይቅርታ፣ በመደጋገፍና በመተሳሰብ አገራዊ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባ ዶክተር ዐቢይ አሳስበዋል። አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅርና የደስታ እንዲሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም