ምክክሩ ለዘላቂ ሰላምና አንድነት መረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ለስኬታማነቱ የድርሻችንን እንወጣለን

136

ደሴ ሚያዚያ 18/2014 ( ኢዜአ) ሊካሄድ የታሰበው ሀገራዊ ምክክር ለዘላቂ ሰላምና አንድነት መረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ለስኬታማነቱ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለፁ፡፡

በኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የዞኑ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ መላከ ገነት ደጀን ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት በአባቶቻችን አጥንትና ደም ዳር ድንበሯ ተከብሮ የተረከብናትን ኢትዮጵያ ሳትደፈር ለትውልድ ማስተላለፍ የኛ ኃላፊነት ነው፡፡

"በተለይ አሁን እንደ ሃገር ከገጠመን ውስብስብ ችግር በዘላቂነት ለመውጣት ሁላችንም በአንድነት ለተረጋጋ ሰላም መስፈን ሚናችንን ልንወጣ ይገባል" ብለዋል።

አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ እምነትና ብሔር ሳይለዩ በሁሉም ላይ አይረሴ ጥፋት ማድረሳቸውን ጠቅሰው፤ "ድርጊቱ ለመጭው ትውልድ እንዳይተርፍ  በሰከነ ሁኔታ እንዲፈታ መረባረብ ይገባል"። ብለዋል ።

ሊካሄድ የታሰበው አገራዊ ምክክር የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና አንድነት ለማረጋገጥ  ወሳኝ በመሆኑ ለስኬታማነቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል ።

"ምክክሩ በሰከነ፣ በተረጋጋና ኢትዮጰያዊ በሆነ የመነጋገር ባህል ተካሂዶ ውጤታማ እንዲሆን በቅንነት ማገዝ ይገባል" ሲሉ አክለዋል።

'ምክክሩ እስከ ታች አሳታፊና አካታች እንዲሆን ህብረተሰቡን አስተባብረን ኃላፊነታችንን እንወጣለን'' ብለዋል፡፡

ሌላው የከሚሴ ከተማ ነዋሪ አቶ ሰይድ ሐሰን በበኩላቸው "ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት ውስብስብ ችግር ተላቃ ዘላቂ ሰላምና አንድነት ለማስፈን ብሄራዊ ምክክሩ ወሳኝ ነው" ብለዋል፡፡

በተለይ የመጠላለፍ፣ የመለያየትና የመከፋፈል ፖለቲካን መልክ በማስያዝ አንድነትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርና አብሮነትን በማስቀጠል  እረገድ ምክክሩ ፋይዳው የላቀ መሆኑን አመልክተዋል ።

''ምክክሩ የታለመለትን ግብ እንዲመታ በምችለው አቅም ሁሉ በማገዝ ኃላፊነቴን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ'' ሲሉ ተናግረዋል።

''ብሔራዊ ምክክሩ  የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም፣ ሰላምና አብሮነት ለማረጋገጥ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው'' ያለው ደግሞ የከሚሴ ከተማ ነዋሪ ወጣት አህመድ ሐሰን ነው፡፡

"ብሄራዊ ምክክሩን በማሳካት እስካሁን ከደረሰብን ችግር ተምረንና አንድነታችንን ጠብቀን አባቶቻችን ያስረከቡንን ሉዓላዊት ሀገር ለትውልድ ለማስተላለፍ እንሰራለን፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም