በአፋር ክልል ከኪልበቲ ረሱ ዞን ለተፈናቀሉ እናቶች አልሚ ምግብና ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደረገ

119

ሠመራ፤ ሚያዚያ 18/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ የሰሜን ምስራቅ አካባቢ ጽህፈት ቤት በአፋር ክልል ከኪልበቲ ረሱ ዞን ለተፈናቀሉ 100 እናቶች አልሚ ምግብና ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ።

አልባሳትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሶችን ያካተተው ድጋፍ ለእናቶች የተደረገው በሠመራ ከተማ ተጠልለው በሚገኙበት አካባቢ ነው።   

ድጋፉን ለተፈናቃዮቹ ያስረከቡት የሠመራ-ሎግያ ከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ አብዱ ሙሳ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የአፋር ህዝብ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን ተሰልፎ  የአሸባሪው ህወሃት ወረራን ለመቀልበስ የድርሻውን ሲወጣ ቆይቷል።

በሂደቱ ቡድኑ በንጹሃን ዜጎች ላይ በፈጸመው ጥቃት ህጻናት ያለአሳዳጊ  ፣ አረጋውያንና አቅመ-ደካሞችም ያለጧሪ ቀርተዋል ብለዋል፡፡

እነዚህን ወገኖች መደገፍ የመንግስትና የተወሰኑ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ብቻም ሳይሆን የሁሉም ህብረተሰብ ክፍል ንቁ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ላደረገው  ከ200ሺ ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ በተጎጂዎቹ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ የሠመራ-ሎግያ አካባቢ ክሊኒኮች አስተባባሪ አቶ አህመድ ሀሰን በበኩላቸው፤  መምሪያው በአፋር ክልል በጦርነት የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት  የድርሻውን እየተወጣ ነው ብለዋል።

ከዚህ በፊት  የተጉዳ አንድ ጤና ጣቢያ መልሶ ወደስራ ማስገባት የሚያስችል እንዲሁም  መድሃኒትና ህክምና ቁሳቁሶችንም ለሌሎች የተለያዩ ጤና ተቋማት ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
 
ዛሬ በሠመራ ከተማ ተጠልለው ለሚገኙ ወገኖች ያደረግነው ድጋፍ የፈሳሽና ደረቅ ሳሙና፣ የሴቶችና ህጻናት ንጽህና መጠበቂ የህጻናት አልሚ ምግብና  አልባሳት ናቸው ብለዋል።

ከተፈናቃይ እናቶች መካከል  ወይዘሮ ኸይሪያ አብደላ፤ ድርጅቱ ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።


ወይዘሮ ሀሊማ ደርሳ በበኩላቸው ፤ ከአሁን በፊትም መንግስትና የአካባቢው ማህበረሰብ እያደረገላቸው የሚገኘው ድጋፍ   ከደረሰባቸው ጉዳት እንዲያገግሙ እንደረዳቸው ተናግረዋል።