ከ11 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጥቷል-ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
ከ11 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጥቷል-ቢሮው

ሆሳዕና ሚያዚያ 18/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ11 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ለ224 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መስጠቱን የክልሉ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የሀዲያ ዞን የኢንቨስመንት ፎረም በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው ።
በመድረኩ ላይ የባለሀብቶች ተሳትፎና የዘርፉ ማነቆ እንዲሁም ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች የተመለከቱ ሀሳቦች ተነስተዋል ።
የደቡብ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀልገዮ ጅሎ በወቅቱ እንደገለጹት የአሰራር ማዕቀፎችን በማደራጀትና በማቀናጀት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ የተሰሩ ስራዎች ውጤት እያስመዘገቡ ነው ።
በተከናወኑ ተግባራት ዘርፉ ለብቻው እንዲመራ መደረጉ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል ።
በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በግብርና፣ በአገልግሎት፣ በኢንዱስትሪ፣ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ዘርፎች ከ11 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ለ224 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መሰጠቱን አስታውቀዋል ።
በዘርፉ በተሰማሩ ባለሀብቶች ጥያቄ ለቀረበላቸው ፕሮጄክቶች ከ11 ሺህ 639 ሄክታር በላይ መሬት በክልሉ ካቢኔ ተፈትሾና ውሳኔ ተሰጥቶበት መተላለፉን አመልክተዋል ።
በዘርፉ ወደ ስራ በገቡ ባለሀብቶች ከ220 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ጠቅሰዋል።
ዘርፉ ውጤታማ እንዳይሆን ማነቆ የሆኑ የሌብነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መቅረፍ የህልውና ጉዳይ ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን በአጽእኖት ተናግረዋል ።
ባለሀብቱ ከመንግሥት ጎን በመሆን በሌብነትንና በመልካም አስተዳደር ችግሮች ከመሳተፍ መቆጠብና ማነቆዎቹን መታገል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በተሰጣቸው ጊዜ ማልማት ያልቻሉ የ19 ባለሀብቶች ፍቃድ መሰረዙን የተናገሩት የቢሮው ሃላፊ መንግስት በሚያመቻቸው ዕድል ተጠቃሚ የሆኑ ባለሀብቶች በጊዜ ወደስራ በመግባት ዘርፉን ከብክነት መጠበቅ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለ26 ባለሀብቶች ፍቃድ መሰጠቱን የገለጹት ደግሞ የሀድያ ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ኢዮብ ጩፋሞ ናቸው።
ባለሀብቶቹ በተሰማሩባቸው መስኮች ከ3 ሺህ በላይ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።
በዞኑ በተሰጣቸዉ ጊዜ ማልማት ያልቻሉ የሁለት ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መሰረዙን ያነሱት ኃላፊው "በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው" ብለዋል።
አስፈላጊውን ሂደት ሳያሟሉ የሚመጡና በተሰጣቸው ጊዜ ወደስራ የማይገቡ ባለሀብቶች መኖራቸውን ጠቁመው ባለሀብቶች መንግስት አሁን ላይ የሰጠውን ምቹ አጋጣሚ በአግባቡ በመጠቀም ራሳቸውንና ሀገራቸውን ሊጠቅሙ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በውይይት መድረኩ ከተሳተፉ ባለሀብቶች መካከል አቶ ማንደፍሮ ባቾሬ ከ10 ዓመት በላይ የደቡብ አፍሪካ ቆይታ በኋላ በሀገር ቤት የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመገንዘብ መመለሳቸውን ተናግረዋል።
በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሰማርተው አካባቢውንና ራሳቸውን ለመጥቀም ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን አንስተው ከመስተንግዶ አንጻር በዘርፉ በሚስተዋሉ አሰልቺ የሆኑ የአሰራር ችግሮች ሊቀረፉ እንደሚገባ አመልክተዋል ።
አሰራሮች ላይ ያሉ ክፍተቶች ቢታረሙ ባለሀብቱ ባለው ልክ በመሰማራት ሀገሩንና ራሱን ጭምር መጥቀም እንደሚችል ገልጸው ከላይ በመንግስት ደረጃ የሚነገሩ የመስተንግዶ አሰራሮች እስከታች ድረስ እንዲወርዱ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል ።
"የኢንቨስትመንት መሰረታዊ ዓላማ አንድ ባለሀብት በወሰደው መሬት ለሌሎች ወገኖቹ የስራ እድል በመፍጠር እራሱንም ሆነ የአካባቢውን ማህበረሰብ መጥቀም ሲችል ነው" ያሉት ሌላው የውይይቱ ተሳታፊና የጆን ፋርም ባለቤት አቶ ዮሐንስ ደገለ ናቸው።
በኢንቨስትመንት ስም መሬት ወስዶ ለታለመለት ዓላማ ማዋል አለመቻል የሀገርንና የህዝብን ተጠቃሚነት አለመረጋገጥ መሆኑን ጠቁመው ድርጊቱን ፈጽመው በሚገኙ ላይ ተገቢ የሆነ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት አመልክተዋል።