ኮሚሽኑ ፍኖተ ካርታና የአፈጻጸም መመሪያዎችን በማዘጋጀት ለቀጣይ ስራዎች ውጤታማነት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

215

ሚያዚያ 18/2014/ኢዜአ/አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ፍኖተ ካርታና የአፈጻጸም መመሪያዎችን በማዘጋጀት ለቀጣይ ስራዎች ውጤታማነት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስገነዘበ፡፡

ኮሚሽኑ በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ያከናወናቸው ተግባራትንም ምክር ቤቱ አድንቋል፡፡

አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እስካሁን ያከናወናቸውና በቀጣይ የሚያከናውናቸው ተግባራት ሪፖርት ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና አመራሮች አቅርቧል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ምክክሩ አራት አበይት ምዕራፎች እንዳሉት ገልጸዋል።

እነዚህም የቅድመ ዝግጅት፣ የዝግጅት፣ የምክክርና ክንውን ሂደት እንዲሁም የምክክር ውጤቶች መተግበሪያ ምዕራፎች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በእያንዳንዱ ምዕራፍ የሚከናወኑ ተግባራትን ዘርዝረዋል።

ኮሚሽኑ አሁን በሚገኝበት የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ የኮሚሽነሮች ትውውቅ፣ አገር በቀል እውቀቶችን ማሰባሰብ መሰነድና ሌሎች ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የውይይት አጀንዳ ቀረጻ ሒደት ልየታና ቅደመ ተከተል፣ የውይይት ጽንጸ ሃሳብ እስከ ታችኛው ማህበረሰብ ድረስ ማስረጽ በዝግጅት ምዕራፍ ከሚከናወኑ ተግባራት ውስጥ ጠቅሰዋል።

በምክክር ሂደት ምዕራፍ ደግሞ ለአገራዊ ምክክር ሂደቱ  ግልጽና አሳታፊ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ከሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ውስጥ መሆናቸውንም ጨምረዋል።

ዘላቂ መፍትሄዎችን መቀመር የምክክር ውጤቶችን በመተግበር ምዕራፍ የሚከናወኑ ተግባራት ውስጥ በማስቀመጥ ለምክክሩ መልካም አጋጣሚዎች፣ ተግዳሮቶችና ጠንካራ ጎኖችንም ለምክር ቤቱ አቅርበዋል ።

የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችና አመራሮች ሪፖርቱ ኮሚሽኑ ስራዎችን በተለያዩ ምዕራፎች ከፋፍሎ በማከናወን በመልካም ጅማሮ ላይ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

የእቅድ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት፣ ለአዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብና መመሪያዎችን መቅረጽ፣ የተግባቦት ስትራቴጂዎችን ማዘጋጀት ኮሚሽኑ በቀጣይ ትኩረት ማድረግ ካለባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንስተዋል።

በምክር ቤቱ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው አገራዊ ምክክሩ ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያን ለመገንባት የተጀመረ ትልቅ ፕሮጀክት እንደሆነ ገልጸዋል።

ምክክሩን እንዲያስተባብር የተቋቋመው ኮሚሽን በየምዕራፉ የሚከናወኑ ተግባራትን በአጭር ጊዜ መለየቱና ስራውን በጥሩ ሁኔታ መጀመሩ ተልዕኮውን ሊያሳካ የሚችልበት ጅማሮ ላይ መሆኑን መገንዘብ ያስችላል ብለዋል።

በመሆኑም ኮሚሽኑ በእያንዳንዱ ምዕራፍ እያከናወናቸው ያሉና በቀጣይ የሚያከናውናቸውን  ተግባራት በግልጽ ለህዝብ ማሳወቅ እንዳለበት አንስተዋል።

ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ የተሰጡ አስተያየቶችን በቀጣይ ለሚያከናውኗቸው ስራዎች በግብአትነት እንደሚወስድ ገልጸው የእቅድ ፍኖተ ካርታው እየተዘጋጀ በመሆኑና በቀጣይ ለምክር ቤቱ እንደሚያቀርቡ አረጋግጠዋል፡፡ 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ ኮሚሽኑ በመልካም አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ የቀረበው ሪፖርት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

የተጀመረውን የእቅድ ፍኖተ ካርታ በፍጥነት ማጠናቀቅ፣ስራዎች የሚመሩበት ደንብና መመሪያ ማዘጋጀት፣ የባለሙያዎች ቡድን ማዘጋጀት በቀጣይ ኮሚሽኑ በትኩረት መስራት ካለበት ጉዳዮች ውስጥ ዘርዝረዋል።

ምክር ቤቱ አገራዊ ምክክሩ በግልጸኝነት፣ ታዓማኝነትና አሳታፊነት እንዲካሄድ ለምክክር ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ አረጋግጠዋል።

አገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የነበራቸው ልዩነት በመፍታት ለዜጎች ምቹ አገር ለመገንባትና ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመሸጋገር የሚያስችል በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም ነው ጥሪ የቀረበው፡፡