በሐረሪ ክልል የኢድ አልፈጢር እና ሸዋል ኢድ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ

282

አዳማ፤ ሚያዚያ 18/2014(ኢዜአ) በሐረሪ ክልል የኢድ አልፈጢር እና ሸዋል ኢድ በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲከበሩ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ።

የክልሉ ፖሊስ ከሚሽነር  ነስሪ ዘከርያ  በሰጡት መግለጫ፤  በክልሉ “ከኢድ እስከ ኢድ”፣የኢድ አልፈጢርና ሸዋል ኢድ በዓላት በሰላማዊ መንገድ እንዲከበሩ በተቀናጀ አግባብ ጸጥታን የማስከበር ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከኢድ እሰከ ኢድ ጥሪ ጋር ተያይዞ ወደ ክልሉ የሚመጡ እንግዶች ሰላማቸው ተጠብቆ  በተገቢው  ለማስተናገድ  ኮሚቴ ተዋቅሮ ዝግጅት እየተደረገ  ይገኛል ብለዋል።

በዓላቱ በሰላም እንዲከበሩ  የክልሉ ፖለስ ከአጎራባች አካባቢዎች፣ መከላከያና የፌዴራል ጨምሮ ከሌሎችም የተለያዩ የፀጥታ አካላት ጋር  በመቀናጀት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም ከጸጥታ ሃይሉ ጋር በጋራ ሆኖ አካባቢውን በመጠበቅ ህብረተሰቡ እየሰጠ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ በመቀጠል አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲመለከት ፈጥኖ እንዲጠቁም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በክልሉ ሁለቱም በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲከበሩ የፀጥታና ህግ አስከባሪ አካላት በመቀናጀት ስራቸውን አጠናክረው እንደሚገኙና በሂደቱ ህግን በሚተላለፉት ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ ኮሚሸነሩ አስታውቀዋል።

በሐረር ከተማ  ሚያዚያ 16 ቀን 2014 ምሽት ላይ  በተለምዶ ሸንኮር አካባቢ ጨለማን ተገን በማድረግ የፀጥታ ችግር በመፍጠር የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም