የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስከበርና እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

532

ሚያዚያ 18/2014/ኢዜአ/ የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስከበርና እኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን 25ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን “ጉዟችን ይቀጥላል” በሚል መሪ ሃሳብ  አክብሯል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ ሚኒስትሮች፣ የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮችና የአካል ጉዳተኛ ማኅበራት ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ወቅት የአካል ጉዳተኞችን መብትና እኩል ተጠቃሚነት ለማስከበር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የአፍሪካ የአካል ጉዳተኞች መብት ፕሮቶኮልን ጨምሮ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ሕግና የኢትዮጵያ ጀግኖች የጦር ጉዳተኞች የተሀድሶና ሥልጠና ማዕከል ማቋቋሚያ አዋጅ ጸድቀው ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮንቬንሽን ተፈጻሚነትና ውጤታማነትን ለማሳደግ ቅንጅታዊ አሰራርን ይበልጥ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ፤ ኮሚሽኑ የአካል ጉዳተኞችን መብት የማስከበርና የማስጠበቅ ሥራን በልዩ ትኩረት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የአካል ጉዳተኞች መብት ላይ የሚሰራ ራሱን የቻለ ዘርፍ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱንም ለአብነት ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ፤ የአካል ጉዳተኞች በሁሉም መስክ ያላቸውን ተሳትፎ ለማጠናከር ፌዴሬሽኑ ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በትብብር መሰራቱን ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ለአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ራሱን የቻለ ዴስክ እንዲዋቀር መወሰኑን የገለጹት ደግሞ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም