የብዝሃ ህይወት ሀብትን ከጉዳት ለመታደግ ስትራቴጂና ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ተገብቷል -ኢንስትቲዩት

285

አዳማ ሚያዝያ 18/2014(ኢዜአ) በሀገሪቱ የብዘሃ ህይወት ሀብት ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳትና የመመናመን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የአስር አመት የስርዓተ ምህዳር ተሃድሶ ስትራቴጂና ፎኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መገባቱን የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይውት ጥበቃ ኢንስትቲዩት አስታወቀ።

ኢንስትቲዩት በብሔራዊ የብዝሃ ህይወት ምክክር ጉባኤ ምስረታና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ እየመከረ ነው ።

በምክክር መድረኩ ላይ  ኢኒስቲቱዩቱ በዘርፉ ያካሄዳቸው የጥናት ግኝት ውጤቶች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ነው ።

የኢትዮጵያ ብዘሃ ህይወት ጥበቃ እንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማሪዮ በወቅቱ እንዳሉት ከምንተነፍሰው አየርና የምንበላውን ምግብ ጨምሮ ያለ ብዝሃ ህይወት ጥበቃ የአየር ንብረት ለውጥን ማስተካከል አይታሰብም።

ባጠቃላይ የሰው ልጅ የህይወት ማእቀፍ ማጠንጠኛም ብዝሃ ህይወት መሆኑን አመልክተዋል።

በዘርፉ ያለውን አሳሳቢነት ለማወቅና ወቅታዊ ምላሽ ለመስጠት ታስቦ የብዝሃ ህይወትና የስርዓተ ምህዳር አገልግሎቶች አሁናዊ መረጃ በማስፈለጉ ብሔራዊ የብዝሃ ህይወት ዳሰሳ ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል።

“የሀገሪቷ የብዝሃ ህይወት ሀብት “እየተመናመነና ጉዳት እየደረሰበት መሆኑን በጥናቱ  አረጋግጠናል” ብለዋል።

በተለይም የውሃና ረግረጋማ መሬቶች ከመጠን በላይ መበከልና መድረቅ፣ የግጦሽ የፖሊሲ አቅጣጫ ላይ የግልፅነት ማነስ፣ ለሀገር በቀል እውቀት የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን፣ መጤ ወራሪ አረምና የግብርና ስነ ምህዳር ላይ እየደረሰ ያለው ተጽእኖ በብዝሀ ህይወት ሀብት ላይ እየደረሰ ላለው ጉዳትና መመናመን ማሳያ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ሀብቱን ካለበት አስጊ ሁኔታ ለመታደግና በዘላቂነት ለሁሉ አቀፍ ልማት ለመጠቀም በአካባቢና ስነ ምህዳር ጥበቃ የባለድርሻዎች የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ኢኒስቲቱዩቱ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የአስር ዓመት የስርዓተ ምህዳር ተሃድሶ ስትራቴጂና ፎኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ወደ ትግባራ መግባቱን  ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

የግብርና ሚኒስትር ተወካይ አቶ ተፈራ ታደሰ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የእፅዋት፣ እንስሳት፣ የደቂቅ አካላትና ሥርዓተ ምህዳሮች መገኛ ከመሆኗ ባለፈ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዋልታ የሆነው የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ  የተመሰረተው በብዘሃ ህይወት ሀብት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ የስራ እድል በመፍጠር፣ በተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪዎች የጥሬ እቃ ግብዓትነት፣ በቱሪዝምና የወጭ ንግድ፣ በባህል መድሃኒትና በግንባታ ጥሬ  እቃነት በሰፊው እያገለገሉ ያሉት የብዝሃ ህይወት ሃብቶች በተለያዩ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች እየተመናመኑና ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የብዘሃ ህይወትና ስርዓተ ምህዳር ተሃድሶ ስራ በሁሉም መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ስራዎች እንዲካተቱ ለማስቻል የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ተሳትፎና ጥረት ወሳኝ መሆኑን ተወካዩ  አስገንዝበዋል ።