በኤርትራና ጅቡቲ መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት የተጀመረው ጥረት ተስፋ ሰጪ ደረጃ ላይ ደርሷል

103
አዲስ አበባ ጳጉሜ 1/2010 በኤርትራና ጅቡቲ መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት የሚደረገው ንግግር ተስፋ ሰጪ ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። በአገራቱ መካከል ያለውን አለመግባባት መፍታት በሚቻልበት መንገድ ላይ የሚነጋገር ልኡክ ዛሬ ጅቡቲ ገብቷል። የልኡካን ቡድኑ የተውጣጣው  ከኢትዮጵያና ኤርትራ ባለስልጣናት ነው ተብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በኤርትራ ቆይታቸው ከተወያዩባቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኛዎቹ አጀንዳዎች  በአካባቢው አገራት መካከል ትስስር መፍጠር እና ቀጠናዊ ሰላምና መረጋጋትን ማምጣት እንደሆነ ተናግረዋል። ከእነዚህም መካከል በኤርትራና ጅቡቲ መካከል ያለው አለመግባባት አንዱ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ረገድ የተካሄደው  ውይይት የተሳካ በመሆኑ ኤርትራ ልኡኳን ወደ ጅቡቲ መላኳን ገልፀዋል። ይህም ኢትዮጵያ በሁለቱ አገራት መካከል ሰላም አንዲመጣ የምታደርገው ጥረት ፍሬ ማፍራቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል። የዚህ ዓይነቱ ጥረት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ካለመረጋጋትና ጦርነት ድባብ ወጥቶ የተፈጥሮ ኃብቱንና የሰው ኃይሉን በአግባቡ በመጠቀም በራሱ አቅም ያለውን የመልማት እድል ያሰፋዋል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል። ይህም እውን ይሆን ዘንድ ኢትዮጵያ በትጋት እንደምትሰራም አረጋግጠዋል። በአሁኑ ወቅት ጅቡቲ የሚገኘው የኤርትራ ልኡክ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ልዩ አማካሪ አቶ የማነ ገብረአብና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኡስማን ሳላህ የተመራ ነው። በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወረቅነህ ገበየሁ የሚመራው የኢትዮጵያ ልዑክም እንደ ሶስተኛ አካል ሆኖ በንግግሩ ላይ እየተሳተፈ መሆኑ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም