የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ43 ቢሊዮን ብር በላይ የገቢ ግብር መሰብሰብ ችሏል

143

አዲስ አበባ  ሚያዝያ 18/2014 /ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ43 ቢሊዮን ብር በላይ የገቢ ግብር መሰብሰብ መቻሉን አስታወቀ።

ቢሮው የ2014 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የእቅድ አፈፃፀም አስመልክቶ ከሰራተኞቹ ጋር ውይይት አካሂዷል።

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተፈራ በዚሁ ወቅት ቢሮው በበጀት ዓመቱ 48 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የገቢ ግብር ለመሰብሰብ እቅድ ይዞ ወደ ስራ መግባቱን አስታውሰዋል።

በዚህም ቢሮው ባለፉት ዘጠኝ ወራት 37 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ፤ 43 ነጥብ 15 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ችሏል ነው ያሉት፡፡

አፈፃፀሙ ከእቅዱ አንጻር 115 በመቶ ሲሆን፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ጭማሪ ማሳየቱን ነው ያነሱት፡፡

የህግ ተገዢነትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራትም መንግስት ሊያጣው የነበረን ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ማዳን መቻሉንም አስረድተዋል።ቢሮው የትኩረት መስኮችን ለይቶ መስራቱ ለአፈፃፀሙ ውጤታማነት አስተዋፅኦ ማድረጉንም ኃላፊው ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ የተቋም አቅም ግንባታ፣ አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ፣ የህግ ተገዢነት ለማረጋገጥ የሚረዱ የማስተማርና የህግ ማሰከበር እንዲሁም ሌሎች ተግባራት ሲከናወኑ ቆየታቸውን ለአብነት አነስተዋል፡፡

በዚህም የስነ-ምግባር ጥሰት በፈፀሙ ከ200 በላይ ሰራተኞች ላይ ከቀላል እስከ ስራ ስንብት የደረሰ እርምጃ መወሰዱንም ገልፀዋል።ህግን አክብረው ሲሰሩ ለነበሩ 299 ግብር ከፋዮች እውቅና እንደተሰጣቸውም እንዲሁ፡፡

“ኢቲ ታክስ” የተሰኘ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በማልማት 298 ሺህ ለሚሆኑ የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ መደረጉን ጠቅሰው፤ አሰራሩን ለማስፋት እየተሰራ ስለመሆኑ አስረድተዋል።

ቢሮው በ16 ቅርንጫፎችና በ17 ንዑስ ቅርንጫፎች አማካኝነት 420 ሺህ ለሚሆኑ ግብር ከፋዮች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም