ሚኒስቴሩ በኦሮሚያ ክልል ድርቅን ለመቋቋም የሚያግዝ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

113

አዲስ አበባ ሚያዝያ 17/2014 /ኢዜአ/ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በኦሮሚያ ክልል ድርቅን ለመቋቋም የሚያግዝ ከ6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አደረገ። 

ድጋፉን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጂነር ሻይሻ መሀመድ ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ አስረክበዋል።    

ሚኒስትሯ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ሚኒስቴሩ በድርቅ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ለመደገፍ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።    

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር በትላንትናው ዕለት ለሶማሌ ክልል ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤ ለኦሮሚያ ክልል ዛሬ የተደረገው ድጋፍም ከዚያ የቀጠለ መሆኑን አብራርተዋል።  

ሚኒስቴሩ ድርቁን ለመቋቋም ለሚደረገው ጥረት 388 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት ተመድቦ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል።  

ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ለእንስሳት መኖ፣ መድኃኒትና የውሃ አቅርቦት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በ150 ሄክታር መሬት ላይ መኖ እየለማ ነው ብለዋል።

እየለማ ካለው መኖ ውስጥ የደረሰው እየተሰበሰበ ድርቅ ባለባቸው አካባቢዎች እየተጓጓዘ መሆኑንም ነው የገለጹት።   

በቆላማ አካባቢዎች የሚገጥመውን የድርቅ አደጋ በዘላቂነት ለመቋቋም በየአካባቢው ያለውን አቅም በጥናት የመለየትና አስፈላጊ ስራዎችን የማከናወን ጉዳይ ትኩረት እንደተሰጠው አብራርተዋል።   

በተለይ አርብቶ አደር አካባቢ ውሃን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ የእንስሳት መኖ ባንክ እስከ ማቋቋም ድረስ ስትራቴጂ ተቀይሶ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።   

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፤ ሚኒስቴሩ ያደረገው ድጋፍ ክልሉ ድርቅን ለመቋቋም የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።   

በክልሉ ያለው አርሶና አርብቶ አደር ውሃ በአግባቡ እንዲይዝና ተጠቃሚነቱን እንዲያረጋግጥ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ነው ፕሬዝዳንቱ ያመለከቱት።  

“የተፈጥሮ ስጦታ አለን፤ ጉልበት አለን፤ በዚህ ላይ ሰርተን የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ መትጋት አለብን።” ነው ያሉት።