ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው – የኢሉ አባቦር አርሶ አደሮች

198

መቱ ሚያዝያ 15/2014 (ኢዜአ) በመኸር እርሻ ሊያጋጥመን የሚችለውን የፋብሪካ ማዳበሪያ እጥረት ለመቋቋም ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው ሲሉ በኢሉ አባቦራ ዞን አርሶ አደሮች ገለፁ።

በዞኑ ለመኽር እርሻ ከሚያስፈልገው የፋብሪካ ማዳበሪያ 53 በመቶ ብቻ መቅረቡን የገለጸው የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽሕፈት ቤት በበኩሉ እጥረቱን ለመቋቋም እስካሁን 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአርሶ አደሮች መዘጋጀቱን አስታውቋል።

የፋብሪካ ማዳበሪያ  በፈለጉት  መጠን  ካለመቅረቡ  በላይ ዋጋውም  ከፍተኛ  ጭማሪ ያሳየ በመሆኑ የምርት መቀነስ  እንዳይገጥማቸው  የተፈጥሮ  ማዳበሪያ  እያዘጋጁ መሆናቸውን የዞኑ አርሶ አደሮች ለኢዜአ ተናግረዋል።

በዞኑ የመቱ አሌቡያ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ግርማ ማሞ እንደገለፁት እንደከዚህ ቀደሙ ለመኽር እርሻ የሚያስፈልጋቸውን የፋብሪካ የማዳበሪያ መጠን ማግኘት አልቻሉም።

ባጋጠመው የፋብሪካ የማዳበሪያ እጥረት ሊከሰት የሚችለውን የምርት መቀነስ ለማስቀረት በቀዬያቸው የተፈጥሮ ማዳበሪያ እያዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል።

ለወደፊትም በተፈጥሮ ማዳበሪያው ላይ ትኩረት አድርገው በመስራት በፋብሪካ በማዳበሪያ እጥረት ምክንያት የሚፈጠረውን የምርት እጥረት ለመቀነስ በግላቸው ዕቅድ እንዳላቸው አርሶ አደር ግርማ አመላክተዋል።

ዘንድሮ የፋብሪካ ማዳበሪያ እጥረት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን የገለጹት ደግሞ ሌላው በወረዳው የወርቃይ ድሬ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ታከለ ዲሳሳ  ናቸው።

የፋብሪካ ማዳበሪያ  ዋጋ በመጨመሩ  ችግሩን  ለመቀነስ  በማሳቸው  ላይ  ከከብቶች  ፍግና ከተለያዩ ዕፅዋቶች ሊያዘጋጁ ወደ ሚችሉት  የተፈጥሮ  ማዳበሪያ  ፊታቸውን  እንዲያዞሩ  እንዳስገደዳቸው ገልፀዋል።

ሌላው የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር ተስፋዬ መርጋ በዘንድሮ መኸር የሚያስፈልጋቸውን የፋብሪካ ማዳበሪያ መጠን  ለወረዳው  ከተሰጠው  ኮታ አንፃር  ማግኘት  እንደማይችሉ  ስለተገለፀላቸው በማሳቸው ላይ 70 ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሚያዘጋጁት የተፈጥሮ ማዳበሪያ በግማሽ ሔክታር መሬታቸው ላይ ለሚዘሩት ሰብል ከበቂ በላይ መሆኑን ጠቁመው ወደ ፊትም ሊገጥማቸው የሚችለውን የፋብሪካ ማዳበሪያ እጥረት ለመቋቋም ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ትኩረት እንደሚሰጡ አመላክተዋል ።

 በተያዘው የመኸር እርሻ የሚያስፈልገው የፋብሪካ ማዳበሪያ የአቅርቦት እጥረትና ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በማጋጠሙ ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ያስታወቀው ደግሞ የኢሉ አባቦር ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽሕፈት ቤት ነው።

በዞኑ ለመኸር እርሻ 103ሺህ 887 ኩንታል የፋብሪካ ማዳበሪያ የሚያስፈልግ ቢሆንም ማቅረብ የተቻለው   55ሺህ ኩንታል ብቻ መሆኑን የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ቻላቸው አዱኛ ለኢዜአ ተናግረዋል።

“በመኽር እርሻ በፋብሪካ ማዳበሪያ እጥረት ምክንያት ሊያጋጥም የሚችለውን የምርት መቀነስ ለማስቀረት አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲያዘጋጅ በግብርና ልማት ባለሙያዎች አማካኝነት የግንዛቤ  ማስጨበጫ ስራ ተሰርቶ ወደ ትግበራ ተገብቷል ” ብለዋል።

እንካሁን ባለው ሂደት  1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአርሶ አደሮች መዘጋጀቱን ነው አቶ ቻላቸው የገለፁት።

በዞኑ በ2014/15 ምርት ዘመን መኸር ወቅት  በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ለመሸፈን ከታቀደው 103ሺህ 887 ሔክታር መሬት ውስጥ 90 ሺህ ሔክታሩ  ታርሶ ቀድመው በሚዘሩ የአገዳ ሰብሎች የመሸፈን ስራ  መጀመሩ አቶ ቻላቸው አስታውቀዋል።